አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዋዌ ኃላፊ የቻይና ግዙፉ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ኩባንያ ህዋዌ አሜሪካ በጣለችው ማዕቀብ ምክንያት ከባድ ፈተና እንደገጠመው ተናገሩ፡፡
ህዋዌ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጉዳዩን ዳግም እንዲያጤነው ጠይቋል፡፡
ትራምፕ ኩባንያው ቻይና ሀገራቸውን ለመሰለል እየተጠቀመችበት ነው በሚል ማዕቀብ እንደጣሉበት የሚታወስ ነው፡፡
እንዲሁም ለሦስተኛ ጊዜ በተሸሻለው ማዕቀብ ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ የአሜሪካ ኩባንያዎች ከህዋዌ ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት አግዳለች፡፡
ይህንን ተከትሎም ኩባንያው የተሻሻሉና ዘመናዊ የሆኑ ቺፕሶችን ማምረት እንደሚያቆም ገልጾ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ምርቱ ከገበያ እንደሚጠፋ ነው ያሳወቀው፡፡
ከማዕቀቡ በኋላ ስጋት የገባቸው የህዋዌ ስልክ ሸማቾች መጨመራቸውንና በአንዳንዶቹም ላይ የዋጋ ጭምሪ ማሳየቱ ተሰምቷል፡፡
ሆኖም ኃላፊው ህዋዌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚያስፋፋው የ5ኛ ትውልድ ቴክኖሎጂ ምንም ተፅዕኖ ሳያርፍበት እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡-አልጀዚራ