ስፓርት

ፌዴሬሽኑ በፖላንድ ለሚካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር አትሌቶችን ለመምረጥ የ15 ኪ.ሜ ማጣሪያ ውድድር በሰንዳፋ አካሄደ

By Abrham Fekede

September 23, 2020

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌዴሬሽን በፖላንድ ጊዲኒያ ጥቅምት 7 ለሚካሄደው የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር የሚሳተፋ አትሌቶችን ለመምረጥ የ15 ኪሜ ማጣሪያ ውድድር በሰንዳፋ መስመር አካሄደ፡፡

ፌዴሬሽኑ በማጣሪያው ላይ አስር ወንድና አስር ሴት አትሌቶች መሳተፋቸው ተናግሯል፡፡

በውድድሩ የተካፈሉት አትሌቶች አምና በሀገር ውስጥ ከተደረገ ግማሽ ማራቶንና በኢንተርናሽናል ባላቸው ውጤት የተመረጡ መሆናቸው ተገልጿል።

መነሻውን ከበኬ ከተማ ወጣ ብሎ ፍፃሜውን ሰንዳፋ ከተማ ባደረገው የ15 ኪሜ የማጣሪያ ውድድር በሴቶች ያለምዘርፍ የኋላ፣ ነፃነት ጉደታ፣ ዘይነባ ይመር፣ አባበል የሻነህ፣ መሰረት ጎላ እና  መድህን ገብረስላሴ እንደየቅድመ ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ስድተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል፡፡

በወንዶች ኃይለማርያም ኪሮስ፣ አንዱዓምላክ በልሁ እና አምደወርቅ ዋለልኝ፣ ብርሃኑ ለገሰ፣ ጉዬ አዶላ፣ ልኡል ገብረ ስላሴ እደየቅድመ ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡

በ2020 ፓላንድ ጊዲኒያ በሚደረገው የአለም ግማሽ ማራቶን ውድድር ባለፈው ዓመት በቢሾፍቱ ማጣሪያ ተደርጎ አትሌቶቹ ሆቴል ገብተው ልምምድ ላይ መቆየታቸውን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡