አዲስ አበባ ፣ መስከረም 12 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሱዳን የሚገኙና በቱሪዝም ዘርፉ የተሰማሩ 26 ባለሃብቶችን የያዘየልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ ነው።
ሱዳንና ኢትዮጵያን በኢንቨስትመንት ተግባራት በማስተሳሰር የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ተናግረዋል።
ከኢንቨስትመንት ተግባራት ባለፈ የዜጎችን የባህል ልውውጥና የጋራ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት ።
ባለሃብቶቹ በአማራ ክልል የሚገኙ ምቹ የልማት ቦታዎችን የሚጎበኙ ሲሆን ተሳትፏቸውም የገበታ ለሀገር አንዱ አካል እንደሆነ አምባሳደሩ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ በበኩላቸው÷የባለሃብቶች ወደ ሀገራችን በተለይም ወደ አማራ ክልል መምጣት የተዳከመውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ያግዛል ብለዋል።
በክልሉ ለኢንቨስትመንት አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን መንግስት እያመቻቸ ነው ያሉት ዶክተር ሙሉቀን በቀጣይም ክልሉ በእቅድ ያሰፈራቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ተቀብሎ ለማስተናገድና ለማስፈፀም መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታቸው አፋር ክልልን፣ ቢሾፍቱንና አርባንጭንም በመመልከት የኢንቨስትመንት አማራጮቻቸውን እንደሚያስቀምጡ ተገልጿል።
በሙሉጌታ ደሴ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።