ቢዝነስ

የሸገር ዳቦ ፋብሪካ የሲቪል ስራው መጠናቀቁ ተገለፀ

By Tibebu Kebede

December 22, 2019

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  ኢ/ር ታከለ ኡማን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከስድስት ወራት በፊት ግንባታው የተጀመረውን የሸገር የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ግንባታ ያለበትን ደረጃ በቦታው በመገኘት ተመለከቱ፡፡

በከተማ ውስጥ ያለውን የዳቦ አቅርቦት ከፍ የሚያደርገውና የዋጋ ንረትንም በተጨባጭ መልኩ ያረጋጋል ተብሎ የታመነበት ይህ ግዙፍ የዳቦ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት የሲቪል ስራው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ በጉብኝቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡

በሀገራችን በዓይነቱ የመጀመርያ የሆነው ይህ የዱቄትና የዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ የማሽን ተከላው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት የሚገባ ይሆናል፡፡

ኢ/ር ታከለ ኡማ የዳቦ ፋብሪካው ግንባታው በፍጥነት ተጠናቅቆ ለከተማችን ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር የከተማ አስተዳደደሩ አስፈላጊ ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

የዳቦ ፋብሪካው ግንባታው ሲጠናቀቅ በሰዓት 80ሺ ዳቦ የሚያመርት ሲሆን ፥ለበርካታ የከተማችን ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡