ዓለምአቀፋዊ ዜና

በምስራቅ አፍሪካ በጎርፍ መጥለቅለቅ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለጉዳት ተዳርገዋል

By Meseret Awoke

September 21, 2020

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምስራቅ አፍሪካ በጎርፍ መጥለቅለቅ ከ 1 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸው ተገለፀ።

ከጎርፍ አደጋው በተጨማሪም በምስራቅ አፍሪካ ካለው የአንበጣ መንጋ ወረርሽን እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በቀጠናው የምግብ እጥረት ስጋት ውስጥ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በአባይ ወንዝ ግማሽ ምዕተ ዓመት ታሪኩ የዝናብ መጠኑ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ሲሆን፥ አብዛኛው የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች ከአየር ንበረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙም ተመልክቷል።

በደቡብ ሱዳን ረሀብ ሊከሰት ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያዎች እየተበራከቱ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በዚያ የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢያንስ ግማሽ ሚሊየን ህዝብን እንደተጎዳ አስታውቋል።

ተጎጂዎችም በወባ፣ ውሃ ወለድ በሽታዎች እና ለተለያዩ ችግሮች በእየተጋለጡ መሆናቸውን ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ተናግሯል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ሃላፊ ማርክ ሎውኮክ በዚህ ሳምንት ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ከዚህ የባሰ ጉዳት ሊከተል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በሱዳን እስካሁን በጎርፍ ምክንያት ከመቶ በላይ ሰዎች ሲሞቱ በኢትዮጵያ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው የሚታወቅ ነው፡፡

ምንጭ፡- ሲ.ጂ.ቲ.ኤን