አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን ያቀናው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው የተመራውና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ያካተተው ቡድን የኦሞ ወንዝን በመስኖ በመጠቀም እየለማ ያለ የሙዝ እርሻን መጎብኘታቸውን የክልሉ የመነግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
በኛንጋቶም ወረዳ በናፕሱመሪያ ቀበሌ በማህበር ተደራጅተው ሙዝ እያለሙ ያሉ ሴቶችን የስራ እንቅስቃሴ የጎበኙ ሲሆን፥ በዚሁ ወቅት “የሙዝ እርሻ እያለሙ ያሉ አርብቶ አደር እንደመሆናችን ከዚህ ቀደም በእርሻ ስራ ላይ ተሳትፎ እያደረግን አልነበረም እናም አሁን መንግስት ባደረገልን ድጋፍ ሙዝ እያለማን ነው” ብለዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ እያለሙት ያለውን የሙዝ እርሻ ስኬታማ ለማድረግ የውሀ መሳቢያ ፓምፕ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
“በመንደር እንድንሰባሰብ ከተደረገ በኅላ የንጹህ መጠጥ ውሃ መጠለያና ተዛማጅ ተግባራት ሊሟላልን ይገባል” ሲሉም ጠይቀዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፥ ከአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በመስኖ ዙሪያ ያጋጠማቸውን ችግር የክልሉ መንግስት እንደሚገነዘበው ጠቅሰዋል።
በቀጣይ የህብረተሰቡን ህይወት ለመቀየር መንግስት የመስኖ ልማት ስራን እንደሚደግፍ በመግለፅ፤ የፓምፕ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
አሁን በስፋት እየለማ ያለውን ሙዝ ወደ የገበያ ለማቅረብ የገበያ ትስስር ለመፍጠርም ድጋፍ እንደሚደረግም ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ አስታውቅዋል።
የተጀመረው የልማት ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስታወቁት አቶ ርስቱ፥ ቀበሌን ከወረዳ የሚያገናኙ መንገዶችን ለመገንባት ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል።