አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ ምሽት 2ሰዓት ከባድ ተሽከርካሪ ማስገባት እና ማንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን የከተማዋ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ።
መመሪያውን ተላልፈው የተገኙ አሽከርካሪዎች ከ500 እስከ 6 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ኤጀንሲው ገልጿል ።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከዚህ ቀደም የከባድ ተሽከርካሪዎችን የሰዓት ገደብ ተግባራዊ ያደረገ ቢሆንም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የሰዓት ገደቡ ላይ ማሻሻያ ማድረጉ ይታወሳል።
በአሁኑ ሰዓትም በሥራ መውጫ ሰዓታት ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅና አደጋን ለመቀነስ እና የከባድ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ማሻሻል የሚያስችል መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉን ኤጀንሲው አስታውቋል።
በዚሁ መሰረት በልዩ ሁኔታ የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ከተሰጣቸው ውጪ ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ ምሽት 2 ሰዓት ከባድ ተሽከርካሪ ወደ ከተማዋ ማስገባት እና ማንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑ ተገልጿል ።
በተጨማሪም በዋና ዋና መንገዶች ላይ ጭነት መጫንና ማውረድ ተግባር የፈፀመ ለመጀመሪያ ጊዜ ብር 1 ሺህ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ብር 2 ሺህ እንዲሁም ከሁለት ጊዜ በላይ ድርጊቱን ከፈፀመ 3 ሺህ ብር ተቀጥቶ የአሽከርካሪው መንጃ ፈቃድ ለአንድ ወር እንዲታገድ በመመሪያው ተቀምጧል ተብሏል ።
በሌላ በኩል ጊዜ ያለፈበት የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ይዞ ወደ ከተማዋ መግባት ወይም በከተማዋ ውስጥ ማንቀሳቀስ ለመጀመሪያ ጊዜ ብር 500 እና ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ብር 1 ሺህ፤ ድርጊቱ ለሶስተኛ ጊዜ ከተፈፀመ ብር 4 ሺህ ተቀጥቶ የአሽከርካሪው መንጃ ፈቃድ ለ2 ወራት ይታገዳል መባሉን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተጨማሪም የተሰረዘ ወይም የተደለዘ ወይም አስመስሎ የተሰራ የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ይዞ መገኘትና መጠቀም እንዲሁም የመንቀሳቀሻ ፈቃዱን ለሌላ አካል አሳልፎ መስጠት 6 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ኤጀንሲው ገልጿል ።
በመሆኑም የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እና ባለቤቶች ተግባራዊ የተደረገውን መመሪያ ታሳቢ በማድረግ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ኤጀንሲው ጥሪውን አቅርቧል ፡፡