Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች የተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡ መስከረም 6 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች የተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ተገልጿል።

በመንግስትና በግል ተቋምና ግለሰቦች ከሚደረገው ድጋፍ በተጓዳኝ የተራድኦ ድርጅቶችም እየረዱ መሆኑ ነው የተመላከተው ።

በዛሬው እለትም የኤልሻዳይ ሪሊፍ እና ዲቨሎፕመንት አሶሴሽን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ለግሷል።

ድርጅቱ ከ300 በላይ ፍራሽና ከ60 በላይ ኩንታል ዱቄትን ጨምሮ የተለያዩ አልባሳትና የምግብ አቅርቦቶችን በክልሉ መንግስት በኩል ለተፈናቃዮች አስረክቧል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አሲያ ከማል በወቅቱ እንደተናገሩት÷ የተፈጠረው ችግር ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

አያይዘውም አሁን እየተደረገ ያለው ድጋፍ ወገን ለወገኑ ፈጥኖ ደራሽ መሆኑን በግልጽ ማረጋገጥ የተቻለበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የኤልሻዳይ ሪሊፍ እና ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቅድስት በቀለ÷ ሁሉን ነገር ለሚሰጥ የአፋር ህዝብ ድጋፉ የሚያንሰው ነው ብለዋል።

በቀጣይም ተመሳሳይ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ መልሶ በማቋቋም ውስጥ የበኩላችንን ሀላፊነት እንወጣለን ሲሉ አረጋግጠዋል ።

በአዋሽ ወንዝ ሰብሮ በመውጣት ምክንያት በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

ወንዙን ወደ ተጥሮአዊ መስመሩ ለመመለስ የፌዴራልና የክልል የኮንስትራክሽን ልማት ድርጅቶች ርብርብ እያደረጉ መሆኑም ነው የተነገረው።

የአፋር ክልል የመንግስት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀጂ ቢዳር ÷ የድርጅቶቹ ኮንስትራክሽን ተሽከርካሪዎች በስፍራው ቀርበው የመስመር ጥገናውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአጭር ጊዜ ስራ ወንዙን መስመር ከማስያዝ በተጓዳኝ ተጎጅዎችን መልሶ ለማቋቋም ከፌዴራልንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በኃይለኢየሱስ ስዩም

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version