አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከክልሎች በሚቀርብ ጥያቄ መነሻነት በጎርፍ አደጋ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እየቀረቡ መሆኑን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ከድርቅ ቀጥሎ በአገሪቱ እየተስተዋለ ባለው የጎርፍ አደጋ ክስተት እስካሁን ከ290 ሺህ በላይ ሰዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን ገልጿል።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ኮሚሽኑ ካለፈው ሚያዝያ ጀምሮ ከብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ ኤጀንሲና ከተፋሰስ ልማት ባለስልጣን በተገኘው መረጃ መሰረት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎች እየተሰራ እንደነበረ ገልጸዋል።
በደጋማ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የጣለው ዝናብ በዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ጎርፍ ማስከተሉን ገልጸው ግድቦች እንዲሞሉ ማድረጉን ተናግረዋል።
ከግድቦቹ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የማፋሰስ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ይህም ሆኖ ግን የጣለው ዝናብ ከመደበኛ በላይ በመሆኑ በተለያዩ ክልሎች የጎርፍ አደጋ ተከስቶ በርካቶች እንዲፈናቀሉ ማድረጉን ገልፀዋል።
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረትም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሆኑ ወገኞች በጎርፍ ጉዳት ሲደርስባቸው ከ292 ሺህ በላይ ደግሞ ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን አመልክተዋል።
ኮሚሽኑ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ያከናወነው የቅድመ ማስጠንቀቂያና አደጋው ከተከሰተ በኋላ በሰጠው ምላሽ የሰው ህይወት ለመታደግ ማስቻሉን ገልፀዋል።
በሄሊኮፕተርና በሞተር ጀልባ በመጠቀም የሰውን ህይወት ለመታደግ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ዜጎች ከክልሎች በሚቀርብ ጥያቄ መነሻነት ምላሽ እየተሰጠ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
የተቀናጀ ስራ በመስራትና ክትትል በማድረግ ድጋፉ ለተጎጂዎች እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ ባቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል የአደጋ ክስተቶችን እየመራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ከፌዴራል በተጨማሪ በክልል ደረጃ በአራት ክልሎች በተቋቋመው ማዕከል የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖርና አደጋዎችን ለመከላከል እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።
የአገሪቱን እድገት የሚመጥን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ስርዓት በመዘርጋት ከአደጋ የተጠበቀ ኅብረተሰብ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ሁሉም እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በዘላቂነት የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ የልማት ስራዎችን መስራት እንደሚገባ መግልጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።