Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፍርድ ቤቱ አቶ ጃዋር ከውጭ አስገብተዋል የተባለውን የሳተላይት መሳሪያ በመትከልና በመደበቅ ክስ የተከፈተባቸውን የአቶ ሚሻ አደም ጉዳይ በሌሉበት ተመልክቷል

አዲስ አበባ ፣መስከረም 6 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቶ ጃዋር መሀመድ ከውጭ አስገብተዋል የተባለውን የሳተላይት መሳሪያ በህገ ወጥ መንገድ በመትከል እና በመደበቅ ህገ ወጥ የቴሌኮም ዝርጋታ ወንጀል ክስ ተከፍቶባቸው የነበሩት አቶ ሚሻ አደም በ20 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ በይግባኝ ተፈቅዶላቸው የነበረ ሲሆን፥ በዛሬው ዕለት አቶ ሚሻ አደም በሌሉበት ጉዳያቸው ታይቷል።

የአቶ ሚሻ አደም ሁለት ጠበቆቻቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በዛሬው ዕለት ቀርበዋል።

ጠበቆቻቸውም የ20 ሺህ ብር ዋሱ ተከፍሎ ደንበኛቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳልተገናኙ እና ያሉበትን እንደማያውቁ ለፍርድ ቤት ገልፀዋል።

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ሳይወሰዱ አይቀርም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ በፅሁፍ አቤቱታ አቅርበዋል።

ጉዳዮን የተመለከተው ፍርድ ቤትም የፌዴራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ ለምን እንዳልፈፀመ፣ ግለሰቡ መለቀቁን ወይም አለመቀቁን እንዲሁም ለኦሮሚያ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን አሳልፎ መስጠቱን ቀርቦ እንዲያብራራ ታዟል።

የኦሮሚያ ክልል ፓሊስ ኮሚሽንም በምን ምክንያት እንደያዘው ቀርቦ እንዲያስረዳ ለመስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ሌሎች ክርክሮችም በቀጣይ ይከናወናሉ ብሏል ፍርድ ቤቱ ።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version