Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኦሮሚያ ክልል የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ትምህርትን ለማስቀጠል እንዲቻል ከ32 ሺህ በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ትምህርትን ለማስቀጠል እንዲቻል 32 ሺህ 108 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፥ በክልሉ ተጨማሪ 30 ሺህ ክፍሎችን ለመገንባት ታቅዶ ከእቅዱ በላይ 32 ሺህ 108 መገንባቱን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ የውሃ እና የመፀዳጃ ቤት ግንባታዎችም መከናወኑንም አስታውቅዋል።

ከመፅሃፍት ጋር በተያያዘም 1 ሚሊየን መጽሃፍት ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የተለያዩ አይነት መጽሃፍቶችን መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

በአጠቃላይ የተሰሩ ስራዎች በክልሉ ህብረተሰብ ተሳትፎ የተሰሩ መሆኑንም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

በቀጣይም የ2013 የትምህርት ዘመን ትምህርት ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር ቶላ ተናግረዋል።

የተማሪዎች ምዝገባም እየተካሄደ ነው ያሉት ዶክተር ቶላ በሪሶ፥ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታትም መዝገባው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

መምህራንን በተመለከተ በክልሉ ከሚገኙ 13 የመምህራን ኮሌጆች 25 ሺህ 300 የ3ኛ ዓመት ተማሪዎችን የማጠቃለያ ቲቶሪያል በመስጠት ወደ ቅጥር ይገባሉ ተብሏል።

በክልሉ በዚህ የትምህርት ዘመን 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሰራተኞች ለገበታ ለሀገር የአንድ ወር ደመወዛቸውን 1 ሚሊየን 249 ሺህ ብር መለገሳቸውም በመግለጫው ላይ ተነስቷል።

በተያያዘ ዜና ከወራት በፊት በሻሸመኔ በነበረው የፀጥታ ችግር ጉዳት ለደረሰበት ሉሲ ትምህርት ቤት የ100 ሺህ ብር እና የተለያዩ የትምህረት ገብአት ቁሳቁሶች በዛሬው እለት ተበርክቷል።

ግብአቶቹን ያበረከተው የኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቢሮ እና የበክልሉ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ማህበር ነው።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ትምህረት በሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ፥ ትምህረት ቤቱ ከ4 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችና 315 ሰራተኞችን ያቀፈ በመሆኑ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በዛሬው እለተም ከ100 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ፣ 69 አይነት 5 ሺህ መጽሃፍቶች፣ 20 ኮምፒውተሮች፣ 50 አረጓዴ ቦርድ፣ 100 ነጠላ ወንበሮች እና 100 ከዴስክ ጋር የተያያዞ ወንበሮች ተበርክተዋል።

የሉሲ ትምህርት ቤት መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ዩሃንስ ወልዴ፥ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ ከቀድሞ በተሻለ ህዝብ ለማገልገል አንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በለይኩን ዓለም

Exit mobile version