አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተያዘው ወር ከሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ ከተማ 1 ሺህ 440 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ መስፍን ገብረማርያም ከመስከረም 6 እስከ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ዜጎችን ከጅዳ ለመመለስ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በዚህም የፊታችን ረቡዕ 300 ዜጎች ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ ብለዋል።
በቀጣይም ቀሪዎቹ ስደተኞች እንደሚመለሱ ያስታወቁት አቶ መስፍን፤ ተመላሾቹ በሕገ ወጥ መንገድ በቀይ ባህር በኩል ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የገቡ፤ በእስር ቤትና በሕገ ወጥ ስደተኞች ማቆያዎች ውስጥ እንደነበሩ አመልክተዋል።
ዜጎቹ ወደ አገራቸው የሚመለሱት በሚኒስቴሩ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣በጅዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት እና የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ተቋም(አይ ኦ ኤም)ጋር በመተባበር እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ባለፈው ሳምንት በሳዑዲ ዓረቢያዋ ሪያድ ከተማ ይኖሩ የነበሩ 147 ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን አቶ መስፍን አውስተዋል።
በቀጣይም በሪያድ የሚገኙ 334 ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ ዳይሬክተር ጄኔራሉ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተጨማሪም ሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም በሊባኖስ መዲና በቤይሩት ወደብ በደረሰው ፍንዳታ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ 132 ኢትዮጵያውያን የፊታችን ሐሙስ ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ዜጎቹ በደረሰባቸው ችግር በመጠለያ ውስጥ የሚገኙና የቲኬት ወጪያቸውም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች እንደተሸፈነም ተጠቁሟል።