አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ተፈጥሮአዊ ፍሰቱን ሰብሮ በመውጣት በግምት እስከ 30 ኪሎ ሜትር ስፍራ ላይ መተኛቱ ተነገረ።
በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ ላይ ሰብሮ የወጣው ውሀ አቅጣጫውን ወደ ማሳና መንደሮች ላይ በማድረጉ የሰብል ጉዳትና የነዋሪዎች መፈናቀልን አስከትሏል።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል ከ136 ሚሊየን ብር በላይ በመበጀት የወንዝ ማስፋትና የዳይክ ጥገና ስራ ቢሰራም የዘንድሮ ክረምት ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መከላከል እንዳልተቻለ አስታውቋል።
በቀጣይ ከክልል መንግስት ጋር በመሆን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወንዙን ወደ ተፈጥሮአዊ የፍሰት አቅጣጫ እንዲመለስ ይደረጋል ተብሏል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ ከሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ከክልሉ ርእሰ መስተዳደር አወል አርባ ጋር በመሆን የደረሰውን ጉዳትና በጉዳቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅትም የአዋሽ ወንዝን በአግባቡ በመጠቀም ጉዳት የማያደርስ ሀብት መሆኑን በተግባር እናሳያለን ብለዋል።
በቀጣይ ሶስት አመታት ውስጥ የወንዙን አቅጣጫ ለመጠበቅ አስተማማኝ መከለያዎችን ከመጠገን በተጓዳኝ ወንዙን ወደ ልማት መቀየር የሚያስችልና የውሃውን ፍሰት የሚጠብቁ አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ዘንድሮ የአዋሽ ወንዝ የሚያደርሰውን ጉዳት ቀድሞ ለመከላከል ጠንካራ ስራ መሰራቱንና የነበረው ክረምት ከተጠበቀው በላይ ሆኖ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሆኖም ጉዳቱ በሰው ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያመጣ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በአደጋው በአፋር ክልል ብቻ 180 ሺህ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን 133 ሺህ ሰዎችን አፈናቅሏል።
አቶ አወል ጉዳት ለደረደባቸው ዜጎች ከግለሰብ እስከ ተቋማት ክፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው ዜጎችን በአጭር ጊዜ መልሶ የማቋቋም ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዛሬው እለትም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከተጠሩ ተቋማት ጋር በመሆን የተለያዩ የሰብአዊ ድጋፎችን አድርጓል።
ድጋፉ በአፋር ክልል ግምታቸው 556 ሺህ ብር በቁሳቁስና 300 ሺህ ብር በጥሬ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በአዋሽ ወንዝ ምክንያት ለተፈናቀሉ 557 ሺህ 844 ብር በቁሳቁስ እንዲሁም 200 ሺህ ብር በጥሬ ድጋፍ አድርገዋል።
በኅይለኢየሱስ ስዩም