አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አዲስ አመትን በማስመልከት 300 ዊልቸሮችን ለአካል ጉዳተኞች አበረከቱ።
የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪዎቹ ኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ ከተባለ ግብረሰናይ ድርጅት የተገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ከዊልቸሮቹ በተጨማሪም ምክትል ከንቲባዋ የበግ ስጦታ ለአካል ጉዳተኞቹ አበርክተዋል።
ወይዘሮ አዳነች ስጦታውን ባበረከቱበት ወቅት እንዳሉት÷ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተዳረጉ አካል ጉዳተኞችን መደገፍ እና መንከባከብ የሁላችንም የዘወትር ተግባር ሊሆን ይገባል ፡፡
የከተማ አስተዳደሩም አካል ጉዳተኞች ያለባቸውን ማህበራዊ እና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡
አካል ጉዳተኞች ትልቅ አቅም እና ጉልበት አላቸው ያሉት ወይዘሮ አዳነች በተለያዩ የሙያ መስኮች ቢሰማሩ ከሌሎች እኩል ውጤታማ መሆን ይችላሉ ነው ያሉት ።
በድጋፍ መርሐግብሩ ላይ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ ፣ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች መገኘታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡