አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።
ኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ፥ በሃገርና ከሃገር ውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለአአዲሱ አመት አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
አዲሱ ዓመት ችግሮችን በአብሮነት መንፈስ በመፍታት የሚታወቀው የሀገራችን ሕዝብ አላስፈላጊ ድርጊቶችን የሚያርምበት ዓመት እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡
መጪው ዓመት ለኢትዮጵያዊያን የስኬት፣ የደስታ እና የብልጽግና እንዲሆን በድጋሚ ተመኝተዋል።
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልም፥ “መጪው ዘመን የሰላም አየር የሚነፍስበት፤ መከባበርና መቻቻል ጎልብቶ ከልባችን ለይቅርታ የምንነሳበት ይሁንልን” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
በጊዜ ሰንሰለት ውስጥ እያለፍን ፤ በኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር አዲስ ዘመን እየተቀበልን እንገኛለን ያሉት ሚኒስትሯ፥ አዲስ ዘመን ሁሌም አዲስ ተስፋ ነው፤ አዲስ ውጥን፣ አዲስ መነሳሳት፣ አዲስ እቅድ፣ አዲስ ስራ፣ አዲስ መንፈስ፣ አዲስ መልካም ነገር ሁሉ እንዲመጣ የምንመኝበት ወቅት ነው ብለዋል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማም በመልካም ምኞት መግለጫቸው፥ “በህብር ውስጥ የኖርን የአኩሪ ታሪክ ባለቤቶች ሕዝቦች ነንⵆመጪው ዘመንም በታሪክ መሀል የተፈጠሩ መዛነፎችን በጥበብ፣ በመቻቻልና በመርህ የምንፈታበትና የምንሻገርበት ይሆን ዘንድ እመኛለሁ” ብለዋል።
“አዲሱ ዓመት ወቅታዊው የጤና ስጋት ተወግዶ ጤናችን ሙሉ የሚሆንበት፣ከራሳችን በላይ አሻግረን ሌሎችን የምናይበት፣ ለሀገራችንና ለወገናችን በቀና ልብ የምንሰራበት፣ ከመጠላለፍ ይልቅ መደጋገፍን የምናስቀድምበት ብሩህ አመት ይሁን” ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።