አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የዘላቂ ልማት ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ።
ማዕቀፉ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ከአውሮፓውያን 2020 እስከ 2025 የሚተገበር መሆኑ ተነግሯል፡፡
የስምምነት ሰነዱን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ተጠሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ ተፈራርመዋል።
አቶ አህመድ በስምምነቱ ወቅት ማዕቀፉ በአገሪቱ ለሚተገበረው የ10 ዓመት ዕቅድ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር ለተካተቱና አገሪቱ ቅድሚያ ለሰጠቻቸው የልማት ጉዳዮችን ይውላል ሲሉ ነው የገለጹት።
ማዕቀፉ አገሪቱ የኮቪድ-19 ወረርሽን እየተዋጋች የልማት ሥራዎችን እየከወነች ባለችበት ወሳኝ ወቅት መፈረሙንም ገልጸዋል።
በማዕቀፉ ለተካተቱት ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች ትግበራ ውጤታማ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፣ መንግሥት የክትትልና ተጠያቂነትን ሥርዓቱን በማጠናከር ማዕቀፉ ውጤታማነት ይሰራል ብለዋል።
በስምምነቱ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር ላሳየው ጠንካራ አጋርነትና ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ችረዋል።
እንዲሁም ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋፅኦ ያደረገ ሲሆን፣ ድጋፉ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር እገዛ እያደረገ መሆኑን አቶ አህመድ አስታውቀዋል።
የግብርናው ዘርፍ ገበያ ተኮር እንዲሆን፣ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲመሰረቱ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የማይተካ ሚና መጫወቱንና መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎትን በተለይ ለችግር ተጋላጭ የኀብረተሰበ ክፍሎች ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እየተመዘገበ ቢሆንም፤ እያደገ ከመጣው የአገሪቱ ፍላጎት አንፃር አሁንም በቂ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ የድህነት ቅነሳ፣ የሥራ ፈጠራ፣ የማህበራዊ አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ማሻሻልና የአምራች ዘርፉን ማልማት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ዶክተር ሶዚ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ልማት ለማገዝ ከአጋሮች ጋር በመተባበር ሃብት በማሰባሰብና ውጤት ለማስገኘት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
በአገሪቱ የልማት ዕቅድና በአገር በቀል የኢኮኖሚ መርሐ ግብሩ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች በተጨማሪ አራት ተያያዥ ጉዳዮች በኢትዮጵያን ዘላቂ የልማት ግቦች መለየታቸውንም ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚደረገው ድጋፍ የኢትዮጵያ በእኩልነት እንዲረጋገጥና አካታች ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ከግቦቹ መካከል እንደሚገኙበት ገልጸዋል።