Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአፋር ክልል በጎርፍ ምክንያት ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ የሸንኮራ አገዳ፣የጥጥ እና ሌሎች ሰብሎች ላይ ጉዳት ደረሰ

አዲስ አበባ ፣ጳጉሜን 3 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ መልቶ ጉዳት ባደረሰበት በአሚባራ ወረዳ የአርብቶ አደሮች፣የግብርና ምርምር እና ባለሃብቶች እርሻ ላይ የደረሰዉ ጉዳት ጉብኝት ተደርጓል፡፡

በጉብኝቱ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን በክልሉ በአሚባራ ወረዳ ኤብሬ ቀበሌን ጨምሮ በ9 ቀበሌዎች ውስጥ በአሚባራ እርሻና በአርብቶ አደሮች ማሳ ላይ የለማ ሰብሎችን በማጥለቅለቅ ያደረሰውን ጉዳት ተመልክተዋል፡፡

ባለሀብቶች እና የአካባቢዉ አመራሮች እንደገለጹት ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ ሰብል የሸንኮራ አገዳ፣የጥጥ እና ሌሎች ሰብሎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በውኃ መጥለቅለቅ ምክንያት ደሴት በሆኑ ጉብታ ቦታዎች ላይ ለተጠለሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም በጀልባ ዕለት ደራሽ ምግቦችን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ የሚገኝ ቢሆንም እርዳታው በቂ ስላልሆነ ትኩረት እንዲደረግ ተጎጂዎች ጠይቀዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ የጉብኝቱ ዓላማ እንደግብርና ሚኒስቴር የደረሰዉን ጉዳት በማየት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት ያለመ መሆኑን አንስተዋል፡፡

እንዲሁም እንደጉዳቱ ሁኔታ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ለሚሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ችግሮችን መለየት አላማ ያደረገ ሲሆን ቀዳሚው ተግባር አቅጣጫውን ስቶ የሚፈሰውን ውሃ ወደ ቀደመዉ መስመር መመለስ እና ለተጎጂዎች የሚደረግ ሰብአዊ ድጋፎች ላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ነው ማለታቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version