አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በክረምቱ በተከሰተው ጎርፍ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወደ 600 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
ሰሞኑን ከተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን፣ ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር፣ ከውኃ ልማት ኮሚሽንና ከአፋር ክልል የተወከሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ የደረሰውን ጉዳት ጎብኝተዋል።
የአዋሽ ወንዝ በቅርብ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ተፋሰሱን አጥለቅልቆ በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
በተፋሰሱ ከሚገኙ አካባቢዎች ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት አንዱ በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ብቻ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
የስራ ኃላፊዎቹ በመተሓራ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ተጠልለው የሚገኙበትን ጊዜያዊ ማቆያና እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን እስካሁን ባለው ሁኔታ እየቀረበ ያለው ሰብዓዊ እርዳታ በቂና በፍጥነት እየቀረበ አለመሆኑንም ነው ተፈናቃዮች የተናገሩት።
ሌላው የአዋሽ ወንዝ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለው አፋር ክልል ዞን አንድ አሚባራና ሃሩካ ወረዳ ሲሆን በወረዳው አሁንም ከባድ የጎርፍ ስጋት ተደቅኗል።
በወረዳው የአዋሽ ወንዝ ተፈጥሯዊ የፍሰት መንገዱን ጥሶ በመውጣት ወደ 16ሺህ ሔክታር የሚሸፍን ሰፋፊ የልማት እርሻዎችን አጥለቅልቆ ነው ከተሞችና መኖሪያ ቤቶችን እስከ መዋጥ የደረሰው።
የክልሉ መንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ አቶ ቢደር አሊ ቢደር እንደተናገሩት ጎርፉ በተለይም አሚባራና ሃሩካ ወረዳ ከባድ ጉዳት አድርሷል።
የጎርፍ አደጋው ከ14 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ሰብልና የመሰረተ ልማቶችን ጨምሮ ከባድ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።
በሄሊኮፕተርና በጀልባዎች ጭምር በመታገዝ ተጎጂዎችን ወደ ተሻለ ቦታ የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎርፉ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ የማቅረቡ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አቶ ቢደር ገልጸዋል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ዳመነ ዳሮታ በበኩላቸው በክረምቱ ከባድ ዝናብ እንደሚኖር እና አደጋውም ሊበረታ እንደሚችል ቀደም ብሎም ግምት ነበር ብለዋል።
በጎርፍ ሳቢያ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ጉዳት እንዲሁም 400 ሺህ ሰዎች የመፈናቀል አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችልም ገምተናል ነው ያሉት።
የክረምቱ ጎርፍ አስካሁን 588 ሺህ ሰዎችን ለጉዳት ሲዳርግ 220 ሺህ የሚሆኑትን ማፈናቀሉንም ገልጸዋል።
መንግስትም በጎርፍ ምክንያት ለጉዳት ለተዳረጉ ዜጎችን ሰብዓዊ እርዳታ እያደረገ ቢሆንም አሁንም ከስርጭት ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉ ብለዋል።
ጎርፉ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም አለመሳካቱን የሚናገሩት ደግሞ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ግዛው ናቸው።
ምንጭ፦ኢዜአ