አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቅዱስ ላሊበላ ከተማ የዓለመ እጽዋት የማደጎ ዛፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
የፕሮጀክቱ መሰረታዊ ዓላማም የቅዱስ ላሊበላን ቅርስ ለመጎብኝት የሚመጡ የውጪ እና የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች የሃገር በቀል ችግኞች እንዲተክሉ የሚያስችል ነው።
በዚህም እንግዶች የሚተክሏቸውን ችግኞች የከተማዋ ነዋሪ በአደራ ተረክቦ የሚንከባከብበት ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፥ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የገነቡ ጠቢባን ልጆች የሆነው ይህ ትውልድ ከዚያ ትውልድ ተምሮ ዛሬም ለሚፈታተኑት ሰው ሰራሽ ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ መነሳት አለበት ብለዋል።
ሚንስትሯ መርሃ ግብሩ የተራቆተውን አካባቢ ዳግም የተፈጥሮ ጸጋውን ከመመለሱም በላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተያዘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የበኩሉን የሚወጣ ነው ብለዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው፥ መርሃ ግብሩ ቅርሱን ለመጎብኝት የሚመጣውን ጎብኚ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የሚያስተሳስር ነው ብለውታል።
በዕለቱም የደን ሃብት ልማትና ጥበቃ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሚል የአማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አለማየሁ ዋሴ የጥናታዊ ጽሁፋቸውን አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የቅዱስ ላሊበላን ቅርስ ጨምሮ ሌሎች ቅርሶች ላይ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ያስችላል የተባለለት የቅዱስ ላሊበላ ቅርስና ቱሪዝም ተቋም በይፋ ለማስጀመር በነገው ዕለት የመሰረት ድንጋይ ይቀመጣል ተብሏል።
ተቋሙ በዘርፉ ለሚደረግ ጥናትና ምርምር የበኩሉን ከመወጣቱም በላይ፤ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት የበኩሉን ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ለመካፈል የፈደራል መንግስት እና የአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በምስክር ስናፍቅ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።