አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ኪት ከአንድ ወር በኋላ ማምረት እንደሚጀመር የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደተናገሩት ኮሮናቫይረስን የመመርመር አቅምን ከፍ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ከአንድ ወር በኋላ ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር የመመርመሪያ ኪት ለማምረት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለእዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ድጋፉን ከምታደርገው የቻይና መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ እየመከሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የመመርመሪያ ኪቱን በአገር ውስጥ ማምረት ሲጀመር ከውጭ የሚገባውን ኪት ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ያሉት ዶክተር ደረጀ ምርቱ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት እንደሚዳረስም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት የኢንፌክሽን መከላከያ ግብዓቶች በኢትዮጵያ በስፋት መመረት መጀመራቸውን ጠቁመው፣ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሶችን ወደ ውጭ አገራት መላክ መጀመሩንም ገልጸዋል።
በሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እነዚህን ቁሶች የሚያመርቱ ኩባንያዎች ቀዳሚ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው መናገራቻን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 52 የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ማዕከላት የሚገኙ ሲሆን በእነዚህም በቀን ከ20 ሺህ በላይ ናሙናዎችን መመርመር ተችሏል።