Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለ’አንድ ጫማ ለአንድ ተማሪ’ መርሃግብር ከ9 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት 24ሺህ ጥንድ ጫማ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስተባባሪነት ለ’አንድ ጫማ ለአንድ ተማሪ’ መርሃግብር ከ9 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት 24ሺህ ጥንድ ጫማ ድጋፍ ተደረገ።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ‘አንድ ጫማ ለአንድ ተማሪ’ በሚል መሪ ቃል ትላንት በተዘጋጀው የሃብት ማሰባሰቢያ መርሐግብር ላይ እንዳሉት በማህበራዊ ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካው ዘርፍ ይበልጥ ተሳታፎ እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።

ሴቶች ካሉባቸው ውስብስብ ማህበራዊ ችግሮች ተላቀው በተለያዩ የሙያ መስክ ተሰማርተው ስኬታማ መሆን እንደሚችሉም በተግባር እያሳዩ እንደሆነም ገልጸዋል።

መርሐ ግብሩ በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና አንድ ጫማ ለአንድ ተማሪ በሚል የተጀመረውን የድጋፍ ንቅናቄ እስከ ወረዳ ባሉ ከ36 ሺህ በላይ የምክር ቤት አባላትን በማስተባበር ለተማሪዎች ምገባ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዘላቂነት እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

በትውውቅ እና ገቢ ማሰባሰብ መርሐግብሩ ላይ በአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስተባባሪነት የ24 ሺህ ጥንድ ጫማ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ይህም በገንዘብ ሲተመን 9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ነው ተብሏል፡፡

በመርሃግብሩ ላይ ሴት አመራሮችን ጨምሮ ሴት ጀነራሎችና የጸጥታ አካላት ፣ ሴት የኪነጥበብ ባለሞያዎች ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች እንዲሁም በተለያየ የሙያ መስክ የተሰማሩ ስኬታማ ሴቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version