Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቀድሞ የሃዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በ2 ቢሊየን ብር ወጪ ወደ ግዙፍ ኢንደስትሪ መንደርነት ሊያድግ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የቀድሞ የሃዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በ2 ቢሊየን ብር ወጪ ወደ ግዙፍ ኢንደስትሪ መንደርነት ሊያድግ ነው፡፡

ፋብሪካው ወደ ጨርቃጨርቅና ኢንደስትሪ ፓርክ ለሚያደርገው ሽግግር ዛሬ ተጨማሪ የማምረቻ ሼዶች ግንባታ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት በይፋ ተከናውኗል፡፡

የማስፋፊያ ግንባታው 14 የማምረቻ ሼዶችን የሚይዝ ሲሆን ግንባታው በ12 ወራት የሚጠናቀቅ ነው ተብሏል፡፡

ዛሬ በተከናወነው የማምረቻ ሼዶች ግንባታ ማስጀመሪያ መረሃ ግብር የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋን ጨምሮ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞን፣ የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ እና የሃዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ተገኝተዋል፡፡

በግል ባለሃብቱ ተሳትፎ ወደ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የጀመረው ፓርኩ፤ በ500 ሚሊየን ብር ወጪ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ግዥ እንደተከናወነለትም ባለሃብቶቹ ተናግረዋል፡፡

ፓርኩ የተሟላ መሰረተ ልማትን አመቻችቶ ከ3 ወራት በኋላ ለተከራዮች ክፍት በማድረግ ምርት እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡

90 በመቶ ምርቱ ለኤክስፖርት የሚሆነው የቀድሞ የሃዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አሁን ወደ ኢንደስትሪ ፓርክነት ሲሸጋገር ሃገሪቱ በምታመነጨው የውጭ ምንዛሪ ላይ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡

ፓርኩ ሙሉበሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ለ35 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

የቀድሞ የሃዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ላለፉት 30 አመታት በመንግሥት ሲተዳደር የቆየ ሲሆን ከ3 አመታት ወዲህ ግን ለሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ተላልፎ አሁን በማስፋፊያ ስራ ላይ ይገኛል፡፡

በሶዶ ለማ

Exit mobile version