አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዳኝነትና የዳኞች ነጻነት መከበር ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ቁልፍ ማዕዘን መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ገለጹ፡፡
የፌዴራልና የክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች አምስተኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
ፕሬዚዳንቷ በዚሁ ወቅት በሀገሪቱ ፍትህና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የዳኝነት ነጻነት መረጋገጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
“የሕግ የበላይነትና ፍትሃዊ ሥርዓት እንዲሁም የዳኝነት ነጻነት ያልዳበረበት አገር በዴሞክራሲም ሆነ በኢኮኖሚ የማደግ ፍላጎቱ ሊሳካ አይችልም” ብለዋል፡፡
የዳኝነት ነጻነት ዳኛው ከማንኛውም አካል ተጽዕኖ፣ ማባበያ፣ ማስፈራሪያና ጣልቃ ገብነት ነፃ በሆነ መንገድ ሕግንና ማስረጃን ብቻ መሠረት በማድረግ እንደሚገለጽ ተናግረዋል፡፡
የዳኝነት ነጻነትበሕግ ማዕቀፍ ብቻ ሳይሆን፤ በተግባርም ጭምር መታየት እንደሚገባው ወይዘሮ መዓዛ ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ነጻነትንና የዳኞች ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንጻር በጀቱ 40 በመቶ ጨምሮ መጽደቁን አስታውቀዋል፡፡
በጉባኤው የዳኝነት ነጻነትን አስመልክተው ጽሑፍ ያቀረቡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሠለሞን አረዳ ዳኞች ከምንም ነገር ነጻ በመሆን ሥራቸውን በሕገ-መንግሥቱ በተሰጣቸው ሥልጣን መሰረት ብቻ ማከናወን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ዳኞች በሁሉም ነገር ራሳቸውን እንዲችሉና ነጻ ሆነው እንዲሰሩ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው መከፋፈላቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የዳኞች ደመወዝ እንዲሻሻልና የትራንስፖርት ሁኔታም እንዲመቻች ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዳኝነት ነጻነትን በፍርድ ቤቱ ሥራ ብቻ የሚረጋገጥ ባለመሆኑም፣ ሁሉም አስፈጻሚ አካላት ከጎኑ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡