አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በ362 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡ 197 ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
የልማት ፕሮጀክቶቹ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እና በክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ካሳሁን እና በሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል፡፡
በምርቃት ስነስርዓቱ አቶ ጃንጥራር አባይ እንደገለጹት ፕሮጀክቶቹ መጪውን የትምህርት ዘመን ለመጀመር የሚያስችሉ ትምህርት ቤቶች እና ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች የህብረተሰቡን ችግሮች ማቃለል የሚችሉ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ጥራት እና ፍጥነት መጠናቀቅ ይኖርባቸዋል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ካሳሁን በበኩላቸው በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑ የልማት ስራዎች መካከል ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ጤና ጣቢያዎች ፣ወጣት ማዕከላት ፣የመስሪያ ሼዶች በጠቅላላው ከ197 በላይ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡