አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት፣ አስፈፃሚ አካላት እና የምርጫ ኮሚሽን ምርጫን በሚመለከት ያወጣው አዋጅ፣ ያሳለፏቸው ውሳኔዎችና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይፀኑ እና ተፈፃሚነት የሌላቸው ናቸው በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ የመጨረሻ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የምርጫ እንቅስቃሴ በተመለከተ የምክር ቤቱ የህገ ምንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ ላይ ዛሬ መክሯል።
ቋሚ ኮሚቴው የህግ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተመልክቶ የራሱን የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።
በኢትዮጵያ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫን በተመለከተ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቀስቀሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ምክንያቶችን በማስቀመጥ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይችል ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ተከትሎ ምክር ቤቱ የቦርዱን የውሳኔ ሀሳብ በመቀበል በጉዳዩ ላይ የህገ መንግስት ትርጉም እንዲካሄድ መጠየቁ ይታወሳል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ምርጫን በወቅቱ ማካሄድ ባለመቻሉ እንዲሁም የምክር ቤቶቹንና እና የአስፈፃሚ አካላትን የስራ ዘመን አስመልክቶ ያቀረበለትን የሕገ መንግስት ትርጉም መሰረት አድርጎ የውሳኔ ሀሳብ መስጠቱም አይዘነጋም።
ያንንም መሰረት በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምርጫን ከማራዘም ጋር በተያያዘ የቀረበለትን የህገ መንግስት ትርጓሜ ጥያቄ ከአተረጓጎም፣ መርህ፣ ዘዴና አላማ ይዘት ጋር ገምግሞ ያቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ምክር ቤቱ አፅድቆ ነበር።
በዚህም መሰረት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በሃገሪቱ ስጋት ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ሁሉም የፌደራልና ክልል ምክር ቤቶች ስራቸውን እንዲቀጥሉ እና ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የጤና ድርጅቶች ኮቪድ-19ኝን በተመለከተ የሚያወጡትን መረጃ መሰረት በማድረግ የጤና ሚኒስቴር፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የሳይንሱ ማህበረሰብ አካላት ወረርሽኙ የህዝብ ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡና ይህም በምክር ቤቱ ከፀደቀ ሃገራዊ ምርጫውን ከ9 ወር እስከ 1 አመት ማካሄድ እንደሚቻል የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቆታል።
ይህንን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያስገድዳል ያለው ዛሬ ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፥ ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ከዚህ ውሳኔ ውጪ በሆነ መንገድ የምርጫ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ፓርቲዎች ቅሬታቸውን ለምክር ቤቱ ሲያስገቡ መቆየታቸው ተመልክቷል።
ክልሉ የምርጫ እንቅስቃሴውን በመቀጠሉና በሂደትም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያደረሰ መሆኑን የሚገልፅ ከተለያዩ አካላት ቅሬታ ቀርበውበታል።
የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ትዴፓ/፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲ ፓርቲና የወልቃይቲ ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ቅሬታ ካቀረቡት ውስጥ ይጠቅስል።
ትዴፓ ክልሉ እያደረገ ያለው የምርጫ እንቅስቃሴ ህገ መንግስታዊ ባለመሆኑ እራሱን ከምርጫው ማግለሉን ገልጾ በሂደቱ ላይ ህገ መንግስታዊ ትርጉም እንዲሰጥበት ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቅርቧል።
የአመልካች የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄና የጉባኤው ስልጣንን በሚመለከት ህግ መንግስቱ የአመልካቹ የትርጉም ጥያቄ አግበብነትን በሚመለከት በአንቀጽ 84 ንኡስ አንቀጽ 2 ስር መብት ይሰጠዋል።
በዚህም የቀረበው የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ በአይነትም በአቀራረቡም የተለየ በመሆኑ ሊታይ መቻሉንም ጠቅሷል።
ህገ መንግስቱ ለክልሎችና ፌደራል መንግስት በተናጠልና በጋራ የሰጣቸው ስልጣኖች በግልጽ የተቀመጡ ሲሆን፥ ምርጫን የሚመለከተው ለፌደራል መንግስት ብቻ የተሰጠ ስልጣን መሆኑን አስቀምጧል።
ምርጫን በሚመለከት ለክልሎች የተሰጠ ስልጣን ባለመኖሩ አንዱ የሌላውን ስልጣን ማክበር እንዳለበት በተቀመጠው ልክ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል።
በስልጣን ላይ የክልልና ፌደራል መንግስት አካራካሪ ጉዳዮች ከገጠማቸው ግን ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ቀርቦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ የሚጸና መሆኑ ተመላክቷል።
ምርጫን የማስፈፀም ስልጣን በህገ መንግስቱ አንቀጽ 51 እና 55 ስር የፌደራሉ መንግስት ስልጣን እንደሆነ አስቀምጧል።
እነዚህ ሁሉ የህገ መንግስት መሰረታዊ መርሆችን በሚቃርን መልኩ የትግራይ ክልል ምክር ቤት የራሱን የምርጫ አዋጅ ማውጣቱን ነው የውሳኔ ሃሳቡ ያነሳው።
ይህ ደግሞ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 102 በግልጽ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር የሚገዳደር ነው ብሏል። የውሳኔ ሀሳቡ ላይም ክልሎች የምርጫ ኮሚሽን የማቋቅም ስልጣን እንደሌላቸው ተንትኗል።
የትግራይ ክልል ምርጫ የማድረግ ውሳኔም ሆነ እንቅስቃሴዎች በተጠቀሱት ህገ መንግስታዊ አንቀጾች መሰረት ተቀባይነት የሌላቸው እንደሆነ ተገልጿል።
የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በዝርዝር የተመለከተው የህግ መንግስት ትርጉም ላይ መሰረታዊ ውሳኔዎችን አስቀምጧልም።
በዚሁ መሰረት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 84 የፌደሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ብሎ የውሳኔ ሀሳቡን አቅርቦ በምክር ቤቱ የህገ መንግስትና ማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተቀባይነት አግኝቷል።
የህገመንግስትና የማንነት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ያቀረበውን ይህንን የውሳኔ ሀሳብ እንዲያፀድቀውም ለምክር ቤቱ ቀርቦ በዝግ ተዋያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ከውይይቱ በኋላም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ በእስከ አሁኑ ሂደት ምክር ቤቱ ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ ክብር ያለው መሆኑንና ህገወጥ አካላት በሚፈፅሙት ድርጊት ምክንያት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም ብሎ የሚያምን መሆኑ እና በቀጣይም ችግሮችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ እና የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች በመጥቀስ የትግራይ ክልል እያካሄደ ካለው ህገወጥ ምርጫ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብት አለማክበር ተቀባይነት የሌለውና ሊታረም የሚገባው መሆኑ አስቀምጧል
ምክር ቤቱ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ያስተላለፈውን ውሳኔ እና የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ በደብዳቤ ሕገ መንግስቱና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲከበር የሰጡትን ማሳሰቢያ አለመቀበሉ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው ብሏል፡፡
በአጠቃላይ ምክር ቤቱ የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔዎች በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን በመጠቆም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012 ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 55(15) እና አንቀጽ 55(2)(መ) ጋር እንደሚቃረን አስታውቋል።
በተጨማሪም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012ን መሰረት አድርጎ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ስልጣን ይጥሳልም ነው ያለው።
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት፣ አስፈፃሚ አካላት እና የምርጫ ኮሚሽን ምርጫን በሚመለከት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012 ያሳለፏቸው ውሳኔዎች እና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይፀኑ እና ተፈፃሚነት የሌላቸው ናቸው በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ የመጨረሻ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል፡፡
በኃይለየሱስ ስዩም