አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ግሪክና ቱርክ በምስራቃዊ ሜዲትራኒያን ውቅያኖስ የድንበር ጉዳይ ላይ እየተወዛገቡ ይገኛሉ፡፡
የውዝግቡ መነሻ ቱርክ በምስራቅ ሜዲትራኒያን ላይ በምታደርገው የኃይል ምንጭ ፍለጋ መሆኑ ይነገራል፡፡
ግሪክም በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የወታደራዊ አቅሟን እንደምታሳድግ በፋይናስ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃለች፡፡
በአንጻሩ ቱርክም የኃይል ፍለጋዋን እያካሄደች የምትገኘው በራሷ ድንበር ላይ መሆኑን ገልጻለች፡፡
የሁለቱ አገራት ውጥረት ተከትሎ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ሴክሬታሪ ጀነራል በትናትናው ዕለት አገራቱ ወደ ጠረጴዛ ቀርበው ችግሮቻቸውን ለመፍታት መስማማታቸውን ይፋ አደርገዋል፡፡
ሆኖም በዚህ መካከል የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት እሰጣ ገባ ውስጥ መግባታቸው እየተነገረ ነው፡፡
ግሪክ ወደ ውይይት ለመግባት ቱርክ የምታካሂደውን ያልተገባ አካሄድ እንድታቆም እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች፡፡
ቱርክ በበኩሏ ግሪክ የሰሜን ጦር ቃልኪዳን በሚያሸማግለው ስምምነት ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት የላትም ስትል ወቀሳዋን ሰንዝራለች፡፡
ሴክሬታሪ ጀነራል በሀገረቱ መካከል ድንገተኛ የሆነ ወታደራዊ ግጭትን ለማስወገድ በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ተስማምተዋል ቢሉም ግሪክ በጉዳዩ ላይ አልተስማማሁም ብላለች፡፡
ሁለቱም አገራት የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን አባል ሀገራት መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ምንጭ፦ሮይተርስ