አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እና መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በመግለጫቸው በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከሳኡዲ ንጉስ እና ከሚመለከታቸው የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት በማድረግ፣ መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል።
በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊውያንን መብት ለማስጠበቅ ከየሀገራቱ ከፍተኛ ሃላፊዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልፀዋል።
በችግር ላይ የሚገኙ እና ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ለሚፈልጉ ዜጎች አስፈላጊው የሰነድ ዝግጅ በመደረግ ላይ እንደሚገኝም አምባሳደር ዲና አብራርተዋል።
በሳምንቱ ውስጥ በሊባኖስ ቤሩት በከፍተኛ ችግር ላይ ይኖሩ የነበሩ 429 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን በመግለፅ ከእነዚህ 165ቱ በተለያዩ አካላት በተደረገ ድጋፍ ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ እንዲመለሱ የተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
በመግለጫቸው የተለያዩ ጉዳዮችን ያነሱት ቃል አቀባዩ የሁለትዮሽ ግንኙት እና ታለቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ውይይቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።
በዚህም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያየያዘ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ላይ መሳተፋቸውን እንዲሁም ከደቡብ ሱዳንን ፕሬዚዳንታዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ንሂያል ደንግንሂያል መወያየታቸውን አስታውሰዋል።
በተመሳሳይ ˝ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኳችን ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል ሁሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎችና የሚሲዮን መሪዎች በተገኙበት ዓመታዊ የአምባሳደሮች ስብሰባ ቀጥሎ እየተካሄደ እንደሚገኝ በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል።
በስብሰባው ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የተደረገውን ሀገራዊ የለውጥ እርምጃ እና በመደመር ፍልስፍና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማሳካት በርዕዮተ ዓለም፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ እንዲሁም በፖለቲካ ዘርፍ በተዘጋጁ ፖሊሲዎች ዙሪያ በሚኒስትሮች ስልጠናው መሰጠቱን አምባሳደር ዲና መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተመሳሳይ በተሻሻለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ውይይት መካሄዱን ፣ የዋናው መስሪያ ቤት እና የሚሲዮኖቸ ዓመታዊ የእቅድ አፈጻጻም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገ መሆኑንና በበጀት አመቱ በተከናወነው የውጭ ግንኙነት ስራ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ተለይተው በቀጣይ የሚስተካከሉ ጉዳዮች አቅጣጫ እንደሚቀመጥ አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አብራርተዋል።