የሀገር ውስጥ ዜና

ዓመቱ በዓባይ ፖለቲካ ላይ ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት ነበር- ምሁራን

By Tibebu Kebede

September 03, 2020

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት ብቻ በቀረው 2012 ዓ.ም በዓባይ ፖለቲካ ላይ ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት እንደነበር ምሁራን ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪ እና የአፍሪካ ጉዳዮች ጥናት መምህር ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ እና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ መምህር አቶ ንጋቱ አበበ፥ ይህ ዓመት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት የተጠናቀቀበት በመሆኑ ልዩ ታሪክ የተመዘገበበት ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ፥ የዘንድሮው የዓባይ ፖለቲካ ስኬት ለቀጣዩ ዓመት ትልቅ ስንቅ  የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲው መምህር ንጋቱ አበበ በበኩላቸው፥ ዘንድሮ ስኬት የተመዘገበው ግድቡን ወደ አዲስ አቅጣጫ በስራ በመቀየር እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ደግሞ ባላንጣዎች የተሞገተበት ዓመት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ባለው የዓባይ ፖለቲካ ላይ ‘‘የራሳችን አሻራ ያለ ማንም ከልካይ ማስቀመጥ የጀመርንበት ዓመት ነበር” ሲሉም ተናግረዋል።

እንዲሁም የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተሰራው ስራ ደማቅ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ግብፅ በኢትዮጵያ የልማት አጋሮች ላይ የምታሳርፈው ተፅዕኖ መኖሩን ያነሱት ምሁራኑ፥ ሰሞኑን የአሜሪካ እንቅስቃሴም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ጉዳዮች መምህሩ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አካሄድ ራሷን አሜሪካን የሚጎዳ እና ሌሎች አፍሪካውያንም ቅሬታ እንዲያነሱ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በሚደረገው ፀረ ሽብር ዘመቻ ግንባር ቀደም መሆኗን አንስተው፤ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አሸባሪው አል ሽባብ አከርካሪው የተመታው በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ምሁራኑ በቀጣዩ ዓመት ከመላው ኢትዮጵያዊያን እና ከዲያስፖራዎች በኩል የሚጠበቅ የቤት ስራ  እንዳለም አንስተዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲው መምህር አቶ ንጋቱ አበበ፥ በቀጣዩ አዲስ ዓመት ገንዘብ ማዋጣቱ ላይ በርትተን የጀመርነውን በፍጥነት ማጠናቅቅ ከቻልን የዲፕሎማሲው መንገድ ቀላል ሊሆን እንደሚችል ተንብየዋል።

በተጨማሪም ተደራዳሪዎች እንደ ከአሁን ቀደሞ ብሄራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቁ ጎዳዮች ላይ የፀና አቋማቸውን አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው አንስተዋል።

በስላባት ማናዬ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።