አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 27 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዐቃቤ ህግ አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ በ14 ተጠርጣሪዎች ላይ ዘጠኝ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን አሰምቷል።
ዐቃቤ ህግ 15 የቅድመ ምርመራ ምስክሮች ማዘጋጀቱን የገለፀ ሲሆን፥ ከ15 ምስክሮች ውስጥ 4ቱ በተለያዩ ምክንያቶች እና የምስክር ጊዜ ላለማራዘም ማሰማት አልፈልግም ሲል ለችሎቱ ገልጿል።
ዐቃቤ ህግ በ11ኛ እና 14ኛ ተራ ቁጥር ያስመዘገባቸው ቀሪ ሁለት ምስክሮች ስልካቸው ባለመስራቱ ለነሃሴ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ከመጋረጃ በስተጀርባ ምስክርነት ይሰማልኝ በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በልደታ አዳራሽ የተገኙት አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቤ ህግ ቀሪ ሁለት ምስክሮች ዛሬ ተሰምተዋል።
በዚህም ሂደትም ዐቃቤ ህግ የሚያሰማቸው እና የማያሰማቸው ቀሪ ምስክሮች ዝርዝር ይገለፅልን ሲሉ የተጠርጣሪ ጠበቆች ጠይቀዋል።
ዐቃቤ ህግም ለደህንነታቸው ሲባል ዝርዝራቸውን አልገልፅም፤ ከዚህ በፊት ምስክር የነበሩ ግለሰብ በተተኮሰባቸው ሽጉጥ ጉዳት ደርሶባቸው ፓሊስ ጣቢያ ማደራቸውን ጠቅሶ በተለያዩ ጊዜ ምስክሮች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰ በመሆኑ ለደህንነታቸው ሲል ዝርዝራቸውን መግለፅ እንደማይፈልግ አብራርቷል።
ተጠርጣሪዎችም የተለያዩ አቤቱታዎቻቸውን ለፍርድ ቤት አስመዝግበዋል።
አቶ በቀለ ገርባ የባንክ ሂሳባቸው መታገዱን እና የግል ተሽከርካሪያቸው እንዳልተመለሰላቸው አቤቱታ አቅርበዋል። እንዲሁም የማረሚያ ቤት አያያዛቸው እንዲስተካከል ጠይቀዋል።
አቶ ሃምዛ አዳነ በአንድ መፅሄት እንዲሁም በሌሎች ጋዜጦች ስሜ እየጠፋ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
አቶ ሸምሰዲን ጠሃ የተባሉ ተጠርጣሪም የጆሮአቸውን ህመም በሚፈልጉት የህክምና ተቋም እንዲታከሙ ፍርድ ቤቱ ያዘዘው ትዕዛዝ አልተፈፀመም ሲሉ በድጋሜ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤትም በተነሱ አቤቱታዎች ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት እና ሁለት የዐቃቤ ህግ ከመጋረጃ ጀርባ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ለነሃሴ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ