አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 27 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የበለስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተንሳፋፊ ሳርና የመለዋወጫ አቅርቦት ስራውን እያስተጓጎለበት መሆኑን የጣቢያው ኃላፊ ገለፁ፡፡
ወደ ጣቢያው የውሃ መቀበያ የሚመጣው ተንሳፋፊ ሳር ለኃይል ማመንጫው የኦፕሬሽን ሥራ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱን ኃላፊው አቶ ፍቃዱ ደምሴ ገልፀዋል፡፡
ተንሳፋፊ ሳሩ ከሐምሌ 9 እስከ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያውን እስከማስቆም ደርሶ እንደነበረ የገለፁት ኃላፊው ባለፈው ዓመትም በተንሳፋፊ ሳሩ ምክንያት ከ10 ቀን በላይ ጣቢያው መቆሙን አስታውሰዋል፡፡
ጣቢያውን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ኤክስካቫተር በመከራየትና ዋና በሚችሉ የጣቢያው ሠራተኞችን በመጠቀም የኃይል ማመንጫውን ውሃ መቀበያ የዘጋውን ተንሳፋፊው ሣር ለጊዜውም ቢሆን በማስወገድ ሥራ ማስጀመር መቻሉን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡
የበለስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ን ከተንሳፋፊ ሳር ለመጠበቅ የሚያግዝ መከላከያ ያለው ቢሆንም በዘንድሮ ዓመት ከሃይቁ ዳር እየተገመሰ የሚመጣው የሳር ደሴት መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ ቀደም ሲል የተገጠመው መከላለያ ሊመልሰው አልቻለም፡፡
በመሆኑም በየጊዜው ወደ ኃይል ማመንጫው ለሚመጣው ተንሳፋፊ ሳር ዘላቂ መፍትሄ ካልተሰጠው በቀር ጣቢያውን እስከ መዘጋት ሊያደርሰው እንደሚችል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት ጀልባ በመከራየት ተቆርሶ የሚመጣውን የሳር ደሴት ለማስወገድ እየተሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ሳሩን ሊያወጣ የሚችል ኤክስካቫተርና ጀልባ በግዢ እንዲሟላ ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ የበለስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ እንደአብዛኛዎቹ ጣቢያዎች የመለዋወጫ አቅርቦት ችግር ያለበት ስለሆነ ችግሩን ለመፍታት ተቋሙ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የበለስ ዘርፈ ብዙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።