በጆርጂያ ጉኔት ኮሌጅ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል አስተማሪ የሆነችው ረዳት ፕሮፌሰር ራማታ ሲሶኮ ሲሴ ሰሞኑን የሰራችው መልካም ምግባር በብዙዎች ዘንድ አስመስግኗታል።
የኮሌጁ ተማሪ የሆነች አንዲት ተማሪ በሚቀጥለው ቀን በመምህርት ሲሴ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ላለመቅረት በማሰብ ህፃን ልጇን ይዛ መማር ትችል እንደሆነ አስተማሪዋን ትጠይቃለች።
ህፃን ልጇን ክፍል ውስጥ ይዛ የምትመጣበት ምክንትም ህፃኗን የምትንከባከብላት ባለሙያ በመታመሟ መሆኑን ታስረዳለች።
የተማሪዋን ችግር በደንብ የተረዳችው ፕሮፌሰር ሲሴም ያለምንም መሳቀቅ ህፃን ልጇን ክፍል ውስጥ ይዛ በመግባት ትምህርቷን መከታተል እንደምትችል በመግለጽ ትፈቅዳለች።
በዚህ መሰረትም ተማሪዋ በሚቀጥለው ቀን በመምህርት ሲሴ ክፍለ ጊዜ ህፃን ልጇን ክፍል ውስጥ ይዛ በመግባት ትምህርቷን መከታተል ትጀምራለች።
ይሁን እንጅ ህጻኑ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ እናቱ ትምህርቷን በተገቢ ሁኔታ እንዳትከታተልና ማስታወሻ እንዳትይዝ ያደርጋታል።
ይህንን ሁኔታ የተመለከተችው መምህርት ሲሴም ተማሪዋ በስርዓቱ ትምህርቷን ትከታተል ዘንድ ህፃን ልጁን ከእናቱ ተቀብላ በማዘል ማስተማር መቀጠሏ ተነግሯል።
ይህ ክፍል ውስጥ የተከናወነ ድርጊት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ መለቀቁን ተከትሎም ብዙዎች መምህሯ ያከናወነችውን መልካም ምግባርና ማህበራዊ ሃላፊነት አድንቀዋል።
ምንጭ፦ ሲ ኤን ኤን