አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 25፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የደቡብ ሱዳን ልዑክን ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
የደቡብ ሱዳንን ልዑክ የመሩት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ንሂያል ደንግንሂያል ናቸው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከልዑካን ቡድኑ ጋር ሀገራቱ በጥምረት በሚሰሯቸው የመሰረተ ልማት ስራዎችና በመንገድ ዘርፍ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በተለይም ሁለቱን ሀገራት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር አጽንዖት ሰጥተው መወያየታቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የጋምቤላ-አኮቦ-ቦር የመንገድ ፕሮጀክትን በጥምረት መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከልዑኩ ጋር መወያየታቸውን በመግለፅ ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ከፍ እንደሚያደርገው ማንሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የልዑካን ቡድንኑን የመሩት ንሂያልም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው የመሰረተ ልማት ዝርጋት በቀጠናው የኢኮኖሚ ትስስርን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡