አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 25፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ከ919 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራምን በመተግበር በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
ፕሮግራሙ እስካሁን ብዛት ያላቸው የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፤ በቀጣይም ፍትሃዊ ተደራሽነትን ባማከለ መልኩ ሰፊ ስራዎች እንደሚያከናውን ተገልጿል፡፡
የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ሃላፊ አቶ ሁሴን መሀመድ የኤሌክትሪክ ኃይል ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ኃይል በማዳረስ የደንበኞች ቁጥር ለመጨመር ቁልፍ ሚና ያለው ይህ ፕሮግራም፤ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ6 ሺህ 759 በላይ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናገረዋል፡፡
ሃላፊው ፕሮግራሙ በዚህ በጀት ዓመት በአዲስና በመልሶ ግንባታ 405 የገጠር ከተሞችና መንደሮች በማገናኘት ከ32 ሺህ በላይ ደንበኞችን ኃይል ለማዳረስ አቅዶ፤ 325 የሚሆኑት የገጠር ከተሞችና መንደሮች በማገናኘት 25 ሺህ 232 አዳዲስ ደንበኞች የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ከመንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ 919 ሚሊየን 277 ሺህ 349 ብር ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ለዕቃ አቅርቦት ግዥ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የኃይል ማሰራጫ ዕቃዎች በተለይ የትራንስፎርመርና የኮንዳክተር ዕጥረት በዋናነት የፕሮግራሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመትም ፕሮግራሙ 450 የገጠር ከተሞችና መንደሮች በማገናኘት 54 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡