አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የአማራ፣ ሶማሌ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የአመራር ስልጠና እየተካሄደ ይገኛል።
የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በባህርዳር የመጀመሪያውን ዙር የአመራር ስልጠና በዛሬው እለት የጀመረ ሲሆን፥ የሶማሌ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ደግሞ በጅግጅጋ ከትናትናው ዕለት ጀምሮ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአመራር ስልጠና ሲጀመር የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደተናገሩት፥ ስልጠናው የሚሰጠው የአመራሩን ውጤታማ የመፈፀም አቅም የማሳደግና በቀጣይም የሚኖሩ ተልእኮዎችን በሚገባ የተረዳ ፤ በፓርቲ ደረጃ ጠንካራ የፓርቲን ግንባታ ማእከል ያደረገ ዲሞክራሲያዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው፥ ስልጠናው በክልሉ የተመዘገበውን ውጤታማ ተግባር ለማጠናከርና ያጋጠሙ ፈተናዎችን ለመቋቋም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያግዛል ብለዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ 6 ቀናት በሚሰጠው የአመራር ስልጠና ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የተመለመሉ 500 አመራሮች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
በተመሳሳይ ብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን በመረዳት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አመራር ለመፍጠር ከትናትናው ዕለት ጀምሮ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
ስልጠናው በትናትናው ዕለት የጀመረ ሲሆን፥ እስክ ነሃሴ 29 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚቆይ ተጠቁሟል።
በመድረኩም የሁለት አመት የክልሉ መንግሰትና የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ሰራ አፈፃፀም ሪፖርት በምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ ሙሰጠፌ ሙሁመድ ዑመርና በፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ኢንጅነር መሀመድ ሻሌ አማካኝነት በማቅረብ ነው የተጀመረው።
ስልጠናው ባለፉት ሁለት ዓመታት የተገኘውን ጥሩ ውጤት ለማስቀጠልና በአንፃሩ የተከሰቱ የለውጥ እንቅፋቶችን ለመቅረፍ የራሱ ሚና እንደሚኖረው ነው የተነገረው።
ከዚህ በፊት የተሰጡ ስልጠናዎች አወንታዊ ውጤት ይዘው መምጣታቸው የተገለፀ ሲሆን፥ የአሁኑ ስልጠና ደግሞ በመንግስትና በፓርቲ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ እንዲያዝ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ተብሏል።
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ለአመራሮች የሚሰጠው ስልጠና የተጀመረ ሲሆን፥ በስልጠናውም 200 የሚሆኑ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራሮች እየተሳተፉ ነው።
ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን በመረዳት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አመራር ለመፍጠር መድረኩ ጠቃሚ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢስቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው፥ ስልጠናው የአመራሮችን በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት በማቃናት የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ስንቅ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤትም ከዛሬ ጀምሮ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናቶች የሚሰጠውን የአመራር ስልጠና በዛሬው እለት ማካሄድ ጀምሯል
የብልፅግና ፓርቲ ደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት “ወቅታዊ ሁኔታዎች እና መሻገሪያ ትልሞች” በሚል ሰነድ ላይ የአመራር ስልጠናው ሀዋሳ ከተማ ላይ ተጀምሯል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እና የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ሀገራዊ ለውጡን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም ያለመውን የአመራር ስልጠና አስጀምረዋል።
ስልጠናው ዓለማቀፋዊ፣ ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ተገንዝቦ የብልጽግና ፓርቲን ተልዕኮ በብቃት ለማሳካት፣ አመራሩን ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ ለማድረግ አቅም እንደሚሆን ተገልጿል።
እንዲሁም እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በጠንካራ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለመመከት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትም ለ5 ተከታታይ ቀናት የሚቆየው የከፍተኛና የመካከለኛ አመራር ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ እንዳሉት ሥልጠናዉ የመሪዎችንና የአባላትን አቅም በመገንባት ለቀጣይ ተልዕኮዎች ዉጤታማ በሆነ መንገድ ለማዘጋጀት ያስችላል ብለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጅሉ በበኩላቸው፥ “የብልፅግና ፓርቲ ግቡ መላው የሀገራችን ህዝብ በአንድነት በማቀፍ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብልፅግና የዜጎች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ያስቻለ ነው” ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤትም ለአመራሮች ስልጠናው መሰጠጥ የጀመረ ሲሆን፥ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነሃሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው ስልጠና ከ300 በላይ የሚሆኑ አመራሮች ተካፋይ ይሆናሉ።
ሰልጣኞቹ ከስልጠናው የሚያገኙትን የአመራር እና የፖለቲካ እውቀት በመጠቀም በቀጣይ የሚገጥሟቸውን ማንኛውም ሁኔታዎች ብቁ አመራር በመስጠት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎችና ችግሮች በአሸናፊነት ለማለፍ የሚያስችል አቅም ልትፈጥሩ ይገባል ሲሉ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መብራቴ ገብረየስ አሳስበዋል።
እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ ሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመጀመሪያ ዙር የከፍተኛ አመራር ስልጠና በዛሬው እለት ጀምሯል።