Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በ11 ግድቦች አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች እንዲነሱና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ግድቦች የሞሉ በመሆኑ የማስተንፈስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የተፋሰሶች ባለስልጣን አሳሰበ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ በሰጡት መግለጫ አስራ አንዱም ግድቦች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የውሀ መሙላት እየተከሰተ ቢሆንም የቆቃ፣ ተከዜ፣ ጣና፣ ጊቤ 3፣ ከሠም እና ተንዳሆ ግድቦች ከመጠን በላይ በመሙላታቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል፣ ከብሄራዊ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና ግድቦቹ ከሚገኙባቸው የክልል አመራሮች ጋር በመሆን አስቀድሞ በተሰራ ስራም አዋሽ፣ አባይ ተፋሰስ እና ኦሞ ላይ ይደርስ የነበረውን የመፈናቀል መጠን መቀነስ መቻሉን ዳይሬክተሯ ገልፀዋል፡፡

በዚህም አዋሽ ላይ 28 ሺህ ሊፈናቀሉ የነበሩ ሰዎችን ቁጥር ወደ 9 ሺህ 310 መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዓባይ ተፋሰስ ላይም በተመሳሳይ 16 ሺህ አባዎራዎች በውሃው የተከበቡ ቢሆንም ምንም አይነት አደጋ እንዳይደርስባቸው ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በተያያዘም በታችኛው ኦሞ ላይ 24 ሺህ 171 ሰው ቀድሞ ከቦታው የማውጣት ስራ በመሰራቱ አደጋውን መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጅ በዘንድሮው ክረምት እየጣለ ባለው ዝናብ ምክንያት ግድቦች በከፍተኛ ሁኔታ እየሞሉ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የማስተንፈስ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሯ የገለጹት፡፡

የማስተንፈስ ሥራው በቆቃ፣ ግልገል ጊቤ፣ ተከዜ፣ ጣና በለስ በተለይም ፎገራና ደንቢያ፣ ግልግል ጊቤ 3፣ መልካ ዋከና፣ ፊንጫ፣ አመርቲነሸ፣ ከሰም፣ መካከለኛው አዋሽ፣ ተንዳሆ፣ ታችኛው አዋሽ እና የገናሌ ዳዋ ግድቦች ላይ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ዋና ዳይሬክተሯ ከእነዚህ መካከል ፊንጫ እና አመርቲነሸ ሥጋት እንደሌለባቸ ጠቅሰው በአንጻሩ ከሰም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያሻው ገልጸዋል፡፡

በትዝታ ደሳለኝ

Exit mobile version