አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲሱ ዓመት ለአስር የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን ፈቃድ እንደሚሰጥ የብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንደገለጹት በቀጣዩ ዓመት ፈቃዱን ከሚያገኙት መካከል በጨረታ ያሸነፉ ሶስት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ይገኙበታል።
እንዲሁም ማስረጃዎችን አሟልተው ያቀረቡ የሳተላይት ጣቢያ ፈቃድ ፈላጊዎች ወዲያውኑ ይስተናገዳሉ ብለዋል።
ፈቃዱ የሚሰጠው ፍላጎትን በማመጣጠንና ያለውን ምጥን የሆነ የአየር ሞገድ ታሳቢ በማድረግ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
የሕትመት መገናኛ ብዙኃንን ለማስፋፋት ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ፈቃድ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመገናኛ ብዙኃን የሚስተዋለውን ያልተገባ አካሔድን በማስከን ዘርፉን ወደፊት በማራመድ ረገድ በኃላፊነት ስሜት መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።
ባለስልጣኑ በዚህ ዓመት ለሶስት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ መስጠቱን ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል።