አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ግብጽ የሙስሊም ወንድማማች ፓርቲን በጊዜያዊነት በመምራት ላይ የነበሩትን ሞሃመድ ኢዛትን በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች፡፡
የ70 ዓመቱ ሞሃመድ ኢዛት ሙስሊም ወንድማማቾችን ከ2013 ጀምሮ በጊዜያዊነት መርተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የዓለም አቀፍ ሙስሊም ወንድማማቾች ሊቀመንበር ናቸው፡፡
የግብጽ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ግለሰቡ በምስራቃዊ ካይሮ ከተደበቁበት ስፍራ በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ነው የተነገረው፡፡
ሚኒስቴሩ በመግለጫው ኢዛት ከ2013 ጀምሮ የፓርቲውን ወታደራዊ ክንፍ መመስረታቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
ግለሰቡ የባለስልጣናት ግድያን በማቀነባበር፣ በመረጃ መረብ ጥቃት፣ ሐሰተኛ ዜናዎችን በማሰራጨትና ባለፈው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንዳታ ተወንጅለዋል፡፡
ሞሃመድ ኢዛት ከዚህ ቀደም በሌሉበት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ነበር፡፡
ምንጭ፣ አል አህራም