አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 21 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴራል የስነምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ንብረታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ 184 ከፍተኛ ባለስልጣናትን ተጠያቂ ማድረጉን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፍቃደኛ ያልሆኑ የመንግስት ባለሥልጣናት ጉዳያቸው በምርመራ ተጣርቶ ክስ እንዲመሰረት ስም ዝርዝራቸውን ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ እና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መላኩን ገልጿል።
ሀብትና ንብረት የማስመዝገብ ግዴታ ያለባቸውን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ በተለያየ ጊዜ በቲቪ፣ ሬድዮ፣ እና በደብዳቤ ጥሪ ባስተላለፈው መሰረት አብዘኞቹ ማስመዝገባቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ይሁን እንጂ በፌዴራልና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር 184 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ኮሚሽኑ ባስቀመጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ ሀብትና ንብረታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ሆነው አለመገኘታቸው ተገልጿል።
ሀብትን ከማስመዝገብ ግዴታ ጋር ተያይዞ ፈቃደኛ ሆነው ያልተገኙ አካላት በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በወጣው የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሰረት ተጠያቂ እንዲሆኑ መደንገጉን አስረድቷል፡፡
በዚሁ መሰረት ኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባ ስራን በማካሄድ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የመንግስት የስራ ሃላፊነትና የግል ጥቅም ሳይቀላቀሉ በየራሳቸው መንገድ የሚመሩበትን ግልጽ ስርዓት እንዲኖር እያደረገ ባለው ሂደት ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ተጠያቂ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን በግለጫው ተጠቅሷል።
በቀጣይም ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ በማይሆኑ የመንግስት ተሿሚዎችና ሰራተኞች ላይ በህጉ መሰረት ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን ኮሚሽኑ ማሳወቁን ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።