አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በውጭ ሀገራት በችግር ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑ ተገለፀ።
በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው እና የሌላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ኖሯቸው በስራ ላይ የነበሩ ዜጎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ስራቸው በመቀዛቀዙ ችግር ውስጥ መግባታቸውንም አምባሳደሩ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሳዑዲ የምግብ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ኮሚኒቲና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር በየቤታቸው ምግብ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ በአገሪቷ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ገልጸዋል።
አምባሳደር ሱሌማን በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ስራ የፈቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመጠለያ እንደሚገኙ እና ባሉበት ሆነው ድጋፍ እንዲያገኙ ከሀገሪቱ መንግስት፣ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ከሌሎች አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለፁት።
በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን መብት ለማስጠበቅ ከአገሪቷ መንግስት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን መግለፃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።