Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም ምክር ቤት ተመሰረተ

የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም ምክር ቤት ተመሰረተ

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 21 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላም ምክር ቤት ዛሬ ተመሰረተ።

ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶችን ቀድሞ ለመከላከል፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የነዋሪውን የሰላም ባለቤትነት ለማረጋገጥ የተቋቋመ መሆኑ ተገልጿል።

በምስረታ ጉባኤው ላይ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ የኃይማኖት አባቶች ፣ ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የምክር ቤቱ መመስረት ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ለከተማዋ እድገትና ብልጽግና ወሳኝ መሆኑም ነው የተነገረው።

በመርሃ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ÷የበርካታ ዓለምአቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው መዲናችን አዲስ አበባ የነዋሪዎቿን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ የምክር ቤቱ መሠረታዊ ተግባር ነው ብለዋል።

የሰላሟ ጠንቅ የሆኑ የምሽት ቅሚያን ጨምሮ የተሽከርካሪ ስርቆት ፣ በቡድን በመደራጀት የህብረተሰቡን ሰላም የማደፍረስ እና ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የነዋሪውን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባ ወይዘሮ አዳነች አሳስበዋል፡፡

ወይዘሮ አዳነች አያይዘውም የከተማዋ ነዋሪ ከምንጊዜውም በላይ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅርበት በመስራት የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ሊያረጋግጥ ይገባልም ብለዋል።

የሰላም ምክር ቤቱ በከተማ ፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ የሚቋቋም ሲሆን÷ ተጠሪነቱ ለከተማው ምክር ቤትና ለከተማው ሰላምና ጸጥታ ቢሮ መሆኑ ተመላክቷል።

በወረዳና በክፍለ ከተማ ደረጃ የሚቋቋሙት ደግሞ ተጠሪነታቸው በየወረዳዎቹ ለሚገኙ የሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤቶች መሆኑን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

Exit mobile version