አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የመገንባት መብቷን በአለም አደባባይ በማሳወቅ እያስመዘገበችው ለሚገኘው የዲፕሎማሲ ድል የዳያስፖራው ማህበረሰብ ጉልህ ድርሻ ማበርከት መጀመሩን በተለያዩ ሀገራት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች አስታወቁ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው በአሜሪካ፣ በቻይና እና በሳውድ አረቢያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደሮቹ ፥ በሀሳብ ሙግቶች የሀገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በእውቀትና በገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል ብለዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አቶ ፍጹም አረጋ እንደተናገሩት፥ አሜሪካ የሚገኙት የዳያስፖራው ማህበረሰብ የድርድር ሂደቱን በማማከር በማህበራዊ ትስስር ድረ ገዖች ዘመቻዎች በማድረግ ድርሻቸውን ተወጥተዋል።
ይህን የንቅናቄ ዘመቻዎች ደግሞ ወደ ገንዘብ ድጋፍ የመቀየር ስራ በኤምባሲው እየተሰራ መሆኑን ያነሳሉ ።
በዋሽንግተን ለመጀመሪያ ጊዜ የገንዘብ ማሰባሰቢያ የሂሳብ ቁጥር ተከፍቶ በአጭር ጊዜ ከ30 ሺህ ዶላር በላይ መሰብሰቡንም አምባሳደር ፍፁም አስታውቀዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አቶ ተሾመ ቶጋም፥ በርካታ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ባለቤት የሆችው ቤጂንግ፤ የተፈጥሮ ሀብትን የመጠቀም መብትን ከራሷ መነጽር ኢትዮጵያን ትይዩ ማየቷን አንስተዋል።
የኢትዮጵያውያንን በራሳቸው ሀብት የመልማት እውነታንም ትገነዘባለች የሚሉት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፥ በግድቡ ግንባታ ላይ የሚደረገው ድርድር የአፍሪካውያንን ችግር በአፍሪካውያን የመፍታት አካሄድንም ያደነቀ ነው ብለውታል።
በቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በእስያ ቀጠና ሀገራት ላይ የሚገኙ ዜጎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ እያስተባበረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የህልውና መሰረታቸው ስለመሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠር በተለያዩ መድረኮች ላይ እየተሳተፉ መሆኑና ድጋፋቸውም ተጠናከሮ መቀጠሉን ተናግረዋል ።
በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አቶ አብዱላዚዝ አህመድ በበኩላቸው፥ በአረብ ሀገራት የተሳሳቱ ትርክቶችን የማረም ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ ስለመሰራቱን ይናገራሉ።
በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የአረብኛ ቋንቋን አንዱ መሳሪያ በማድረግ አባይን የመጠቀም መብትን ዙሪያ እና ግድቡ ጉዳት እንደማያደርስ የግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች መከናወኑን ገልጸዋል።
የዳያስፖራው ማህበረሰብ የኢትዮጵያውያን በአባይ ወንዝ በፍትሃዊነት የመጠቀም እውነታዎችን የማስረዳት ሙግታቸው ቀጥሏል ያሉት አምባሳደሮቹ፥ የግድቡ ግንባታ እንዲጠናቀቅ ደግሞ የገንዝብ ድጋፋቸው እንዲጠናከርም እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሀይለኢየሱስ መኮንን
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።