አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አብዛኛው ኢትዮጵያውያን የህገ መንግስት ማሻሻያና ተጨማሪ የፌደራል የስራ ቋንቋዎች መኖርን እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች የሚስማሙ መሆኑን የአፍሮ ባሮ ሜትር ጥናት ውጤት ጠቆመ።
የአፍሮ ባሮ ሜትር ጥናት 8ኛው ዙር የጥናት ውጤት ይፋ ተደርጓል።
በጥናት ውጤቱም ኢትዮጵያውያን የኢፌዴሪ ህገ መንግስት እንዲሻሻል፣ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች እንዲካተቱ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ዘመን እንዲገደብ በሚሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚስማሙ፤ በሌሎች መመዘኛዎች ላይ ግን ልዩነት ማሳየታቸውንም ነው ጥናቱ የጠቆመው።
በጥናቱ መሰረትም የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አሁን ባለው ቢቀጥል ወይስ ቢሻሻል በሚለው ላይ ከጥናቱ ተሳታፊዎች 68 በመቶዎቹ መሻሻል አለበት ያሉ ሲሆን፥ 18 በመቶዎቹ ባለበት ቢቀጥል፤ 11 በመቶ ደግሞ በአዲስ መተካት አለበት ማለታቸውን ጥናቱ አመላክቷል።
ለፌዴራል መንግስት ተጨማሪ የስራ ቋንቋ ማድረግ/ማካተት በሚለው ላይም ከጥናቱ ተሳታፊዎች ውስጥ 73 በመቶዎቹ ተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎች ቢካተቱ እንደሚስማሙ ሲገልፁ፤ 3 በመቶዎቹ ባለበት እንዲቀጥል ያሉ ሲሆን፥ 24 በመቶዎቹ ደግሞ ተቃውመውታል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የስልጣን ዘመን በሁለት የምርጫ ጊዜ መገደብን በተመለከተም 68 በመቶዎቹ እንደሚደግፉት፣ 23 በመቶዎቹ እደሚቃወሙ እና 9 በመቶዎቹ ደግሞ ድምጽ አልሰጡበትም።
ገለልተኛ የሆነ የህገ መንግስት ፍርድ ቤት ማቋቋም የሚለውንም 55 በመቶ የደገፉ ሲሆን፥ 25 በመቶ ተቃውመውታል፤ 21 በመቶ ደግሞ ሀሳብ አልሰጡበትም።
የጥናቱ ተሳታፊዎች በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለውን ማስወገድ፣ በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ መሀል ላይ ያለውን አርማ ማስወገድ እንዲሁም አዲስ አበባም የፌዴሬሽን አባልነት ማካተት የሚለውን በአብዛኛው የጥናቱ ተሳታፊዎች የተቃወሙት ሲሆን፥ ጥቂቶቹ ደግፈውታል።
እንዲሁም የጥናቱ ተሳታፊ ኢትዮጵያውያን በፌዴራሊዝም ስምምነት ቢኖራቸውም ብሄርን መሰረት ያድርግ ወይስ መልክአ ምድር አቀማመጥን የሚለው ላይ ልዩነት እንዳላቸው ጥናቱ አሳይቷል።
ጥናቱ በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተደረገ እንደሆነና ሳይንሳዊ መለኪያዎችን በመጠቀም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ በፌደራሊዝምና ህገ መንግስት ጉዳዮች ላይ መደረጉ ተነግሯል።
አፍሮ ባሮ ሜትር አፍሪካ ላይ ትኩረት ያደረገ ገለልተኛ የሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን የሚሰራ ተቋም ነው።
በተስፋዬ ከበደ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።