አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር የቀጣይ አመት የትምህርት ምዝገባን ከነሃሴ 20 ቀን ጀምሮ ማካሄድ እንደሚቻል አስታወቀ።
የትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሃረጓ ማሞ ትምህርት ቤቶች ምዝገባውን ሲያካሂዱ ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል የተቀመጡ መከላከያዎችን በሚገባ በመተግበር መሆን አለበት ብለዋል።
ትምህርት የሚጀመርበት ቀን በቀጣይ እንደሚወሰንና ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡
የቀጣዩ አመት የትምህርት ሂደት ስኬታማ እንዲሆንም ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆችና መላው የትምህርት ማህበረሰብ የሚተላለፉ መልዕክቶችን በመከታተልና ቫይረሱ ሊተላለፍ የሚችልባቸውን መንገዶች ከወዲሁ በማስወገድ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
አካላዊ ርቀትን ጠብቆ ለማስተማር፣ የንፅህና መጠበቂያዎችን ከማዘጋጀትና መሰል የኮሮና መከላከል ተግባራትን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ቀድም ብለው ዝግጅት የሚደረግባቸው ተግባራት መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጊዜን በተመለከተ ሚኒስቴሩ በቅርብ የሚያሳውቅ ሲሆን ተማሪዎች ራሳቸውን እያዘጋጁ እንዲቆዩ መልዕክት ማስተላለፉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።