የሀገር ውስጥ ዜና

የስነ ምግባር ችግር በታየባቸው የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ እርምጃ ተወሰደ

By Tibebu Kebede

August 24, 2020

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 18፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ህገ መንግስቱንና የህዝብን ሰላም በመጠበቅ ሂደት ውስጥ የስነ ምግባር ችግር በታየባቸው የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ የእርምት እርምጃዎች መውሰዱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የ2012 ዓ.ም የስራ አፈፃፀሙን እየገመገመ ሲሆን በዚህም የፖሊስ ሰራዊቱ ህገ መንግስቱንና የህዝብን ሰላም ከማስከበር አኳያ ውጤቶች ማስመዝገቡ ተጠቅሷል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው እንደተናገሩት ሰራዊቱ በሃገሪቱ የሚያጋጥሙና ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሰላም መደፍረሶችን በመከላከልና ከተከሰተ በኋላም በማረጋጋት በኩል የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል።

በተለይም በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ደህንነታቸው እንዲረጋገጥና ግንባታቸው እንዳይቋረጥ ከመጠበቅ፣ ጥፋተኞችን ለህግ ከማቅረብ አኳያ ከሌሎች የሃገሪቱ የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

ይሁን እንጅ በዓመቱ በነበረው የፀጥታ ማስከበር ሂደት ውስጥ በሰራዊቱ ውስጥ ያጋጠሙ የስነ ምግባር ክፍተቶችን ኮሚሽኑ መገምገሙንም ተናግረዋል።

በግምገማውም የተወሰኑ አባላት ከተሰጣቸው ሃላፊነትና ግዴታ ውጭ በመንቀሳቀስ ሚስጥርን ለሌላ አካል አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርሱ ጥፋቶች ይፈጽሙ እንደነበርም ማወቅ ተችሏል ብለዋል።

ይህን ተከትሎም ማጣራትና ግምገማ በማካሄድ ጥፋተኝነታቸው በተረጋገጠ የፖሊስ አባላት ላይ ህጋዊ የእርምት እርምጃ መወሰዱንም ነው የተናገሩት።

እርምጃው ከቀላል የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ማባረር የደረሰ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኮሚሽነር ጄኔራሉ በበጀት ዓመቱ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ለላቀ ግዳጅ መዘጋጀት አለብን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ በበኩላቸው ባለፈው በጀት አመት የህዝቡ ሰብዓዊ መብት ሳይነካ ህገ መንግስቱንና የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ ጥረት ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም ሰራዊቱን መሳሪያ ለመንጠቅ የመሞከርና በአንዳንድ ቦታዎች የመንጠቅ አዝማሚያዎች ማጋጠማቸውን ገልፀው ይህም ሆኖ ባለፈው ስርአት የነበረውን ተጠርጣሪንና ወንጀለኛን የማሰቃየት፣ የመደብደብና መሰል የሰብዓዊ መብቶች ሳይነኩ ወንጀለኛን ለህግ ከማቅረብ አኳያ ጥሩ ስራ መሰራቱን አውስተዋል።

በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከሰው ሃይል እጥረትና ከአንዳንድ የፀጥታ ማስጠበቂያ ግብዓት ውስንነት ጋር ተያይዞ ግጭት ሲፈጠር ፈጥኖ በቦታው ያለመገኘት ችግሮች እንደነበረም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የግብዓት እጥረቶቹ እየተፈቱ መሆናቸውንና የሰው ሃይል በማሰልጠን፣ ያለውን የፖሊስ ሰራዊት በአግባቡ በመቅረፅና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በማቀናጀት ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።