የሀገር ውስጥ ዜና

ዓመታዊው የአምባሳደሮች ስብሰባ ተጀመረ

By Tibebu Kebede

August 24, 2020

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዋናው መስሪያ ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች እና ቆንስል ጀኔራሎች ዓመታዊ ስብሰባ ቢሾፍቱ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

ስብሰባው “ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኳችን ለሃገራዊ ብልጽግናችን” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ ያለው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መስሪያ ቤቱ በበጀት አመቱ በአዋጅ የተሰጠውን ሃገራዊ ሀላፊነት ለመወጣት በውጭ ግንኙነት ፖሊሲው የትኩረት መስክ መሰረት በርካታ ስራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሃገራት በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን፣ በሱዳን የተፈጠረው ቀውስ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር እንዲኖር፣ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር እንዲሁም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት በመፈራረምና በቀጠናው ሰላም የማስከበር ስራዎች ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱን አንስተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ለአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር፣ በኢጋድ ማዕቀፍ በክልሉ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስርን በመፍጠር፣ በሃገራችን ሰላም፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ከሚገኙ ሃገራት ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት በማድረግ ነባር እና አዳዲስ ስትራቴጅክ አጋሮችን በማፍራት በሃገራችን እየተካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ድጋፎች እንዲያገኝ በማድረግ አወንታዊ ስራዎች መሰራታቻውን ጠቅሰዋል።

በተለይም ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በድርድር ሂደት የተገኘውን ድል በፐብሊክ ዲፕሎማሲ በማጀብ የሃገራችን አቋም የሆነውን ፍትሀዊና ምክንያታዊ የተጠቃሚነት መርህን ለማስረዳት እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለመሰብሰብ የረዳ ጠንካራ የገፅታ ግንባታ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በባለ ብዙ መድረኮችና በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ዘርፍም በበጀት አመቱ በርካታ አበረታች ስራዎች ማከናወኑንና በሚቀጥለው ዓመትም ከዚህ በተሻለ ለመስራት ስብሰባው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ስብሰባው ሁሉም አምባሳደሮች በተገኙበት በአካል እየተካሄደ ሲሆን የኮቪድ19 ወረርሽኝን በመከላከልና የጤና ፕሮቶኮል መርህን መሠረት በማድረግ የስብሰባው ዓለማ ግቡን እንዲመታ ሁሉም ተሳታፊ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባውም ጥሪ አቅርበዋል።

በስብሰባው ላይ የለውጥ ሥራዎች እና የመደመር ፍልስፍና መሰረታዊ ሀሳቦች፣ የፖለቲካ ብልጽግና እና የመደመር ገጽ፣ የኢኮኖሚ ብልጽግና እና የመደመር ገጽ፣ የሃገሪቱ የቀጣይ የአስር ዓመታት መሪ የልማት ዕቅድ፣ የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤዎች በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ፣ ስትራቴጂክ አመራር እና የውጤት ተኮር ዕቅድ አስተቃቀድ ስልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡

እንዲሁም የእያንዳንዱ ኤምባሲ የ2012 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀምና ሪፖርት ግምገማና በልዩ ልዩ ሃገራዊ፣ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ የውጭ ግንኙነት ፈታኝ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የጋራ ግንዛቤ እንደሚያዝ ይጠበቃል።

ስብሰባው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 20 12 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።