Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኤርትራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ባህል ቡድን የመጀመሪያ የሙዚቃ ዝግጅቱን በከረን ከተማ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኤርትራ የሚገኘው የኢትዮጵያ የባህል ቡድን የመጀመሪያ የሙዚቃ ዝግጅቱን በከረን ከተማ አቅርቧል።

በትናንትናው ዕለት በከረን ስታዲየም በተካሄደው በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት የብሄራዊ ቲያትር የሙዚቃ ክፍልና ታዋቂ ድምጻዊያን የተለያያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እና ዘመናዊ ሙዚቃ እንዲሁም ጨዋታዎችን ለከተማዋ ነዋሪዎች አቅርበዋል።

በተጨማሪም የባህል ቡድኑ ከከረን ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘውን በ2ኛው የአለም ጦርነት ወቅት ለሁለት ወራት የአሊያንስ ፓወር እና ፋሺስት ጣልያን የተዋጉበት እንዲሁም 23 ሺ የሚጠጉ ወታደሮች ያረፋበትን ጡቁሉአስ ተብሎ የሚጠራውን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ጎብኝተዋል።

በዚህም በጦርነቱ ወቅት የአሊያንስ ሀገራት እና የጣሊያን እና ከጣሊያን ጎን የተሰለፋ ወታደሮች ያረፋበትን የመቃብር ስፍራ እና የጣሊያኑ ጀነራል ሎራንዶ ሎረንስ የመቃብር ስፍራ መጎብኘታቸውን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ቲያትር፣ ከታዋቂ ደምጻውያንና የጃኖ ባንድ ሙዚቀኞችን ያካተተው የኢትዮጵያ ባህል ቡድን ኤርትራ መግባቱ ይታወሳል።

የባህል ቡድኑ ጉዞ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተፈጠረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው።

ቡድኑ ለአንድ ሳምንት በኤርትራ የሚቆይ ሲሆን፥ ከከረን በተጨማሪ በምፅዋ ከተማ የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።

Exit mobile version