አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) 10ኛው የኢትዮ ሩሲያ ወታደራዊ እና ቴክኒክ ትብብር ስብሰባ በሞስኮ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የውይይቱ ዓላማ በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ያለውን ወታደራዊ እና ቴክኒክ ትብብር ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ልዑክ መሪ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሌላ አለም ገብረዬሃንስ እና የሩሲያ ልዑክ መሪ አናቶሊይ ፑንቹክ ውይይቱን እየመሩት ይገኛል፡፡
በዚህ ወቅት ሚኒስትር ደኤታዋ አምባሳደር ሌላ አለም ባደረጉት ንግግር ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት የወታደራዊ እና ቴክኒክ ትብብር ያደነቁ ሲሆን ኢትዮጵያ ይህን ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ዝግጁነት ገልፀዋል፡፡
የሩሲያ የፌዴራል ወታደራዊ እና ቴክኒክ ትብብር ምክትል ዳይሬክተር አናቶሊይ ፑንቹክ በበኩላቸው የኢትዮጵያና ሩሲያን ጠንካራ ግንኙነት ያደነቁ ሲሆን ይህን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡