አዲስ አበባ፣ታህሳስ 8፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ)በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባው የእናቶችና የህፃናት ማዕከል በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመር ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባውን የእናቶችና የህፃናት ማዕከል እንዲሁም በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና መስሪያ ቤት የተገነባውን የህክምና ግብዓቶች ማከማቻ ማዕከል ያሉበትን ሁኔታ ጎብኝተዋል።
በዚህም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ የተሰራው ባለ 8 ፎቅ እና 450 አልጋ የሚይዝ ምቹ የእናቶችና የህፃናት ማዕከል ግንባታ የተጠናቀቀ መሆኑን እና በቅርቡተመርቆ ስራ የሚጀመር መሆኑን ዶከተር አሚር ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና መስሪያ ቤትም ከ2 እስከ 8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ቅዝቃዜ ለሚያስፈልጋቸው የህክምና ግብዓቶች ማከማቻ የሚሆንኑ 6 ቀዝቃዛ ክፍሎች መገንባታቸውን ነው የገለጹት።
በተመሳሳይም ከ25 እስከ 15 ድግሪ ሴንቲግሬድ ቅዝቃዜ ለሚያስፈልጋቸው የህክምና ግብዓቶች ማከማቻ የሚሆኑ ሁለት የከፍተኛ ቀዝቃዛ ክፍሎች ግንባታ መጠናቀቁንና ወደ ስራ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸው ተመላክቷል።
ዶክተር አሚር ለተከናወነው ስራ ስኬት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና በኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የሚሰሩ አመራሮች እና ሰራተኞችን አመስግነዋል።