የሀገር ውስጥ ዜና

ግራንቪል ኢነርጂ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚፈልግ ገለጸ

By Mikias Ayele

March 22, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግራንቪል ኢነርጂ በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ማዕከላት ግንባታና ባትሪ ምርት ላይ መሰማራት እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ በርኦ ሃሰን ከግራንቪል ኢነርጂ ኤክስኪቲቭ ኦፊሰር ታቢ ቲ ታቢ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው በአረንጓዴ ትራንስፖርት በተለይም በተሽከርካሪና ሌሎች በኤሌክትሪክና በፀሐይ ሃይል በሚሰሩ የዘርፉ ግብዓቶች ዙሪያ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

አቶ በርኦ ሃሰን÷ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት በመንግስትና በግሉ የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዘርፉን ለመደገፍ አበረታች ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው ÷ በዘርፉ መሰማራት ፍላጎት ካላቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡

ታቢ ቲ ታቢ በበኩላቸው÷ግራንቪል ኢነርጂ በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ማዕከላት ግንባታ እና ባትሪ ምርት ላይ መሠማራት እንደሚፈልግ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡