አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሲዲሲ ባደረጉት ጉብኝት ያመላከቱን አቅጣጫዎች ለአህጉሪቱ የጤና ስርዓት መጠናከር ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው ሲሉ የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዢያን ካሴያ ገለጹ።
የአፍሪካ የጤና ስርዓት ህልውና ለሆነው አፍሪካ ሲዲሲ መጠናከር መሪዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካ ሲዲሲን በዛሬው ዕለት መጎብኘታቸው ይታወቃል፡፡
በጉብኝታቸውም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ የማኅበረሰብ ጤና ተቋም የሆነው አፍሪካ ሲዲሲ መቀመጫ በመሆኗ ክብር ይሰማታል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዢያን ካሴያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ለማዕከሉ ሰራተኞች ደስታንና በበለጠ ትጋት እንድንሰራ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአካል በመምጣት ድጋፋቸውን ማሳየታቸውና ማዕከሉን ወደፊት የሚያራምዱ አቅጣጫዎች መስጠታቸው አስደሳችና ለሌሎች መሪዎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የአፍሪካ ሲዲሲ የላብራቶሪ አቅሙን በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ሀገራትን በተሻለ ለማገልግል በከፍተኛ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ መሪዎች ማዕከሉ የጤና አገልግሎትን እንዲያስፋፋ በሙሉ ኃላፊነት እንዲተባበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ ስለማቅረባቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡